ልዕልት ሆይ

1 min read
article-banner-img

ተረቶቻችንን ምን ያህል ተረድተናቸው ይሆን?

"ድሮ ልጅ እያለው የምወደው ተረት ነበር። ልዕልቷ እና እንቁራሪቱ። ብዙ ግዜ ነበር ያነበብኩት። ጥንቅቅ አድርጌ። ጓደኛዬ እንዴት እንደ እንቁራሪት ያለ አስቀያሚ እና ቀፋፊ እንሰሳ ይሳማል ትለኝ ነበር። ይሰቀጥጣት ነበር። እኔ ግን ከእንቁራሪትነቱ በላይ ተቀይሮ ልዑል መሆኑ ያስደስተኝ ነበር። ጉዞው ሳይሆን ውጤቱ ይማርከኝ ነበር። በመጨረሻም ከልዑሉ ጋር መጋባት! ያንን ተመኝቼ ነበር ከእሱ ጋር የሆንኩት። ምንም የሚያስከፉኝ ባህሪያት ቢኖሩትም፣ ምን አስቸጋሪ ቢሆን፣ አንድ ቀን ይቀየራል ለእኔ ሲል ይስተካከላል ለእኔ ብሎ ይሻላል። ያኔ ይህን አስቤ ባልታገሰው እስከ ወዳኛው ልዑሌን አጣዋለው ብዬ ፈርቼ ነበር። ብቻ ይህን እና ያንን ብዬ ብዙ ታገስኩ፣ ጠበኩ ግን ልዑሌ አልመጣም። ባይ ባይ ያው የቀድሞው እንቁራሪት ነው። ይቀየራል ብዬ የጠበኳቸው ነገዎች እንደዋዛ ትላንቶች ሆነዋል። ለውጥን ሳይሆን እውነታን አሳዩኝ።"

ዛሬ ደሞ በጠዋቱ ምን ይሆን የምታሰማኝ? በሰላም አውለኝ ብዬ አልጸለይኩም እንዴ? ተረት. . . እንቁራሪት ምን ጉድ ነው። " ዙፋኔ ተረጋጊ እስኪ! በጠዋቱ ምን እያልሽኝ ነው? አሁንም ከአምሃ ጋር ተጣላቹ? ቆይ ግን እናንተ ሰላም የምትሆኑት መቼ ነው?" ሳይቸግረኝ አስተዋውቄ እንዲ ዕዳ ልግባ ሆሆሆ።

"አንቺ አልተረዳሺኝም ለእሱ ታደያለሽ አይደል? እኔ እንደተሸወድኩ ነው ሚሰማኝ፣ ተታልዬ እንደገባሁ። ለዚህ ራሴን አላዘጋጀሁም። መቼ እንዲ ሆኖ ይቀራል ብዬ አሰብኩ?" እንባዋ መውረድ ጀመረ። ሁሌም የኔ እና የዙፋን የውይይት ርዕስ አምሃ ነው። እሱ እንዲ አድርጎ እሱ እንዲ ብሎ እሱ እዛው ቀርቶ. . . . .የዛሬው ግን መረር ያለ ይመስላል። "እሺ በቃ ቀስ ብለሽ ንግሪኝ። ምን ሆናቹ ነው?"

"ታውቂው የለ ምንም ብል ጭቅጭቅ ነው። ጀመራት ደሞ ይለኛል። ለእኔ ብሎ ለፍቅር ብሎ አንድም ነገር ማድረግ አይፈልግም። እሱ እና የእሱ ህይወት ብቻ ነው የሚታየው። የሱ ስራ የሱ ችግር የሱ ኑሮ ይቀድማሉ። እኔ ግን የለሁም።"

"ዙፋኔ እሱ ድሮስ እንዲ አልነበር እንዴ? አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?" ይህንን መልስ ስሰጣት ዛሬ ለትሪሊየኛ ጊዜ ይመስለኛል። አምሃ እንዲ ነው። ከምንም እና ከማንም በፊት የራሱን ምቾት የሚያስቀድም ሰው ነው።

"አዎ የማላውቀው አዲስ ነገር የለም ግን ደግሞ ለእኔ ሲል ይቀየራል፣ ለፍቅራችን ሲል ትንሽም ቢሆን ወደ እኔ ይጠጋል ብዬ አስብ ነበር። አሁን ሳየው ግን ወዴትም አይቀየርም ወዴትም። አየሽ ተሸወድኩ በገዛ ፍቃዴ እና ፍላጎቴ ተስፋን እና ከንቱ ተረት ይዤ የህይወትን ቁማር ተበላሁ።" እንባዋን በጠዋት ማየቱ ይረብሸኝ ጀመር። ለዚ ምን ይባላል? መልስ መስጠት እንዳለብኝ ተሰማኝ። " በቃ እሺ ዙፋን አታልቅሽ። እኔ አናግረዋለው እስኪ ምን እንደሚለኝ ሰምቼ እነግረሻለው። ሃሳብሽን አስረዳዋለው። ዝም በይ በቃ።" በሁለቱ መሃል መልዕክት አቀባባይ እንደመሆን እና ለማስታረቅ እንደመታገል የሚሰለች ምንም የለም።

"ሄሎ አምሃ ደህና አደርክ?"

"ደህና ነኝ እመቤት እንዴት ነሽ?" የአምሃ ድምጽም ደስ አይልም። ውይ ፈጣሪዬ በጠዋቱ ምን ውስጥ ገባሁ?

"አልሁልህ እኔማ ከዙዬ ጋር አሁን አውርቼ ትንሽ ስለከፋት ላውራክ ብዬ እኮ ነው።" ዙዬ ብሎ ነው ሚጠራት ያው እንደዛሬው ካልተናቆሩ። "ታውቃልህ በሁለታቹ መሃል መግባት ብዙም ደስ እንደማይለኝ ግን መፍትሄ ካለ አብረን እንፈልግ ብዬ ነው።" ምን አለ እሺ ብሎ የምትፈልገውን ቢያደረግ. . .ደረቅ

"እመቤት አንቺ እንዴት እንደማይሰለችሽ አላውቅም። እኔ ግን በቅቶኛል፣ ትክት ነው ያለችኝ። በየቀኑ ተመሳሳይ ንትርክ ሁሌ አንድ አይነት ጭቅጭቅ ኤጭ. . በዛ። እኔ እንደዚ ነኝ፣ ይኸው ነኝ። ወዴትም ልቀየር አልችልም። ለማን ብዬስ ነው ምቀየረው?" ለሷ ብለህ ብለው ደስ ይለኝ ነበር ግን የሰው ቤት ሊጥ ማብኳት መስሎ ተሰማኝ። " ያው ለፍቅር ብለህ አምሃ ምን አለበት?"

" ውውው. . . እመቤት እንዲ ያለ ነገር አታውሪብኝ። ፍቅር ምናምን የሚባል አዛ ቡዜ ማውራት አያስፈልግም። አንቺም ብትሆኚ ፍቅር ምናምን እያልሽ መንዘባዘብሽን ብትተይ ይሻልሻል።ይህ የደሃ ለቅሶ ነው። ምኑም የማያምር ከንቱ ጩኸት። እሷ ቆይ ምን ይሁን ነው ምትለው? ምን ስለተበደለች ነው ወይስ ያልሆንኩትን ነኝ ማለት ነበረብኝ? ይኸውልሽ እመቤት እኔ እንደውም ከዚህ ወዲያ ይህን ጉዳይ ማውራት አልፈልግም። በቃ! አምሃ ይህ ነው ካላስ! ተቀየር ተቆረጥ ፊላን ፊል የሚባል ነገር አልሰማም። ንገሪያት እውነታውን አውቃ ተቀብላ ትኑር" ሃሳቡን ለማስቀየር አይደለም የምለውን ለመስማትም ፈቃደኛ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። "እሺ ለማንኛውም በአካል ተገናኝተን እናወራለን አምሃ ተወው በቃ።"

"ምንም አናወራም እመቤት ለማንኛውም ቻው።"

ከአምሃ ቁጣ አዘል ንግግር ውስጥ የያዝኳቸው ጥቂት ቃላት ነበሩ። 'እውነታ፣ መቀየር' ማሰብ ጀመርኩ። ዙፋን ስለምትወደው ተረት ስታወራኝ ነበር። ልዕልቷ ስትስመው ወደ ልዑልነት ስለተቀየረው እንቁራሪት። ዙፋን ያልገባት ግን አምሃ የሚቀየረው እንቁራሪት አይደለም። በእርግማን እና በሁኔታዎች ተገዶ አይደለም እንቁራሪት የሆነው በምርጫዎቹ እንጂ። የእሷ መጽሃፍት ዓለም በብዙ አይነት እንቁራሪቶች እንደተሞላች አልነገሯትም። ከእኚህ እንቁራሪቶች መሃል ልዑሎቹ በጣም ጥቂት ናቸው። ምናልባትም በጣት የሚቆጠሩ ብቻ። የአምሃ እንቁራሪትነት እንዳለ ሆኖ ከዙፋንም አንድ የጎደለ ነገር ነበር።

ያቺ ልዕልት እንቁራሪቱን ስትስመው ልዑል ይሆናል ብላ ሳይሆን የእውነት ወዳው ነው፣ እንቁራሪትነቱን ተቀብላ። ከአስቀያሚ መልኩ አልፋ የመውደዷ ሽልማቷ ደግሞ ወደ ልዑልነት መቀየሩ ነበር። እንቁራሪት ቢሆንም ወደ ልዑልነት ባይቀየርም ለእሷ በቂ ነበር። አምሃ ፍቅር ፍቅር አትበይ ቢለኝም የሁሉም ነገር መነሻ እና መጨረሻ ፍቅር ነበር።

ለዙፋን ሄጄ ምን ልበላት? ልዑሉ አይመጣም አርፈሽ እንቁራሪትሽን ታቅፈሽ ኑሪ ልበላት ወይስ ፍቅርን ብለሽ ሳይሆን ምኞትሽን አስበሽ ስለመጣሽ ሽልማትሽን አጥተሻል?Comments (1)
No comments yet