ባለድርሻ

ድባቴ (መደበር) ምንድን ነው? ምን ምን መገለጫዎች አሉት
ድባቴ
"ቀኑ ሲደብር..."
"ሁሉም ነገር አስጠልቶኛል..."
"ምርር ነው ያለኝ..."
"ብሞት ነው ሚሻለው..."
" ማንም ሰው አይረዳኝም..."
በዙሪያችን ያሉ ሰዋች አልያም እኛው እራሳችን እነዚህን እና መሰል ቃላቶችን በየዕለት ተዕለት ኑሮአችን ውስጥ ስንጠቀመው እንስተዋላለን። የዓለም ጤና ጥበቃ ተቋም እ.ኤ.አ በ 2019 ባጠናው ጥናት መሰረት ዓለማችን ላይ ከ280 ሚሊየን ሰዋች በላይ በዚህ የድባቴ ስነ-ልቦናዊ ህመም ወይም ቀውስ ሲሰቃዩ ይስተዋላሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአብዛኛው በዚህ በሽታ የሚጠቁ ወጣቶች እና አዛውንቶች ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በብዙ ምክንያቶች ሰዎች በተስፋ መቁረጥ እና የተለያዩ ጭንቀቶች ውስጥ በመግባት በቀላሉ በእንደዚህ ዓይነት የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ በመግባት ራስን እስከማጥፋት ደረጃም ድረስ ይደርሳሉ።
ታዲያ በየመንደራችን ውስጥም "እገሌ እኮ በጭንቀት እራሱን አጥፍቶ ሞተ" የሚሉ ዜናዎች ለጆሮ አዲስ መሆናቸውን ካቆሙ እና የኛም ድንጋጤ ጋብ ማለት ከጀመረ ሰነባብቷል!
በዚህ በድባቴ በሽታ ራስን ወደማጥፋት ደረጃ የሚደርሱ ወጣቶች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱም ለብዙ የጤናው ባለሙያዎች ስጋትን እየፈጠረ መቷል! የዚህ ሁሉ ግን መሠረቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ ችግሩ አስከፊነት እና ምንነት ዕውቀት ማነስ ወይም ጠቅላላውኑ ግንዛቤ አለመኖር ናቸው!
ድባቴ (depression) ምንድነው?
ያልተለመደ እና ከፍተኛ የሆነ የዓዕምሮ ህመም ሲሆን የሠዎች አስተሳሰብ ላይ አሉታዊ የሆነ ስሜትን እና ባህሪን በመፍጠር ሰዎች የየዕለት ኑሮአቸውን ማከናወን እስኪያቅታቸው ድረስ ከፍተኛ ለሆነ ጭንቀት መጋለጥ ማለት ነው።
ነገር ግን በአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ስለበሽታው ግልፅ የሆነ ግንዛቤ ካለመኖር እና ከቸልተኝነት የተነሳ በዚህ የስነ-ልቦና ህመም የሚሠቃዩ ሰዎች ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም።

የድባቴ ህመም በጠቅላላው በአምስት የሚከፈል ቢሆንም ከአምስቱ አንዱ ማለትም
"Major depressive disorder" በአብዛኛው የሚስተዋል ነው።
ከብዙው በጥቂቱ ስለ በሽታው መገለጫዎች!
- ከፍተኛ የሆነ ሀዘን፤ ማልቀስ፤ ባዶነት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲስተዋል።
- ንዴትን መቆጣጠር አለመቻል፤አብዝቶ ዝም ማለት(ብቸኝነትን መምረጥ)፤ አለመረጋጋት ወይም ምንጩ ያልታወቀ የፍርሀት ስሜት መኖር።
- የመደበኛ የህይወት እንቅስቃሴዎች ላይ ስሜት ወይም እርካታ አለመኖር።
- የእንቅልፍ ችግር (እንቅልፍ ማጣት ወይም አብዝቶ መተኛት )።
- ምንም ዓይነት ተግባርን ሳይከውኑ አልያም በትንንሽ ተግባራት የመድከም እና አቅምን የማጣት ስሜት።
- ቀሰስተኛ የሆነ ንግግርን ማድረግ፤ በአንድ ሀሳብ ላይ አለመርጋት ወይም ለማሰብ መቸገር።
- ዋጋ የለኝም ብሎ ማሰብ፤ ምክንያቱ በግልፅ ያልታወቀ የፀፀት ስሜት እና ባለፈ ታሪክ እና ትውስታ መጨነቅ/ማብሰልሰል።
- የአካል ክብደት መለወጥ ( ውፍረት መጨመር ወይም መቀነስ)።
- ከፍተኛ የሆነ ራስን የማጥፋት ሀሳብ እና ሙከራዎችን ማድረግ።
መቼ ወደ ባለሙያ መሄድ ይኖርቦታል?? ከላይ የተጠቀሱትን መገለጫዎች ሁለት ሳምንት እና ከዛ በላይ ካስተዋሉ እና እነዚህ ምልክቶች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ችግር እየፈጠረቦት ከሆነ የስነ-ልቦና ባለሙያ ያማክሩ።
ይህ የስነ-ልቦና ቀውስ የስንቶቻችንን ቤት እያንኳኳ ነው?
ስንቶቻችንስ ነን ይህን ዓይነት የአዕምሮ ህመም ስናስተውል መዳን እንደሚችል የስነ-ልቦና ህመም ምንረዳው? ወይም ከእርኩስ መንፈስ ጋር የምናገናኘው?