ትንሹ አምላክ
አንዳንድ ነገሮች
እንደው ድንገት እልፍ ስትሉ በሆነ አጋጣሚ እንኳን የፀጋዬ እሸቱን 'ሆዴ ክፉ ዕዳዬ' የሚለውን ሙዚቃ ሰምታችሁ ታውቁ ይሆን? ለስለስ ቀዝቀዝ ያለ፣ዕንባውን የቀረበ ካለም አልቅሱ አልቅሱ የሚል የሆድን ባዳነት በሰባት ደቂቃ ባነሰ ዜማ ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ሙዚቃ ነው።
አዝማቹ ሆዴ ክፉ ዕዳዬ ነው ይላል። ሲራብ አሳደርኩት ሆድ ጠግቦ አይጠግብምና ዳግም እህል ዉሃ አለኝ። እኔም የገዛ ገላዬን በማጣት ውስጥ ሆኜ ታዘብኩት ብሎ ይጀምራል። የሆድ ክፋቱ በቃኝ ብሎ አለመጥገቡ ፤ ሲያጣም ጊዜ አለመስጠቱ ነው። ምንም እንኳን እኛ በየቀኑ ለመጥገብ ብዙም ዕድሉ ያለን ህዝብ ባንሆንም የዘመናት ችግራችን ግን ይህን አፉን የከፈተ 'ቅድም በላው በቃኝ' የማይለውን ሆዳችንን ማስታገስ ነው። የሰው ልጅ ሆድ ልክ እንደምናሳድገው እንደምናስታምመው አነስ ያለ አውሬ ነው። ጥጋቡም ትዕቢትን፣ ረሀቡም ጭካኔን ያመጣል።
በቀጣይ ግጥሙ ላይ የሰው ፊት እንደእሳት እየገረፈው እንደሚለምን እና ቀን ለማይሰጠው ሆዱ ትንሽ ነገር ለማቅመስ እንደሚሽቆጠቆጥ ያስረዳል። ያው ይህ የአብዛኞቻችን እውነታ ነው። የሰው ፊት እያየን የምንለፋው የምንደክመው የዕለት ጉርስ ቁራሽ እንጀራ ፈልገን ነው። በመስሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤትም ይሁን በመኖሪያ ቤት ሳንፈልግ ተገደን ላይ ታች የምንለው ሆድ የተባለውን አለቃችንን ዝም ለማስባል ነው። ያው ዞሮ ዞሮ የማንሰግድለት ተሸክመነው የምንዞረው አምላካችን ሆኗል። ግን ያሳስባል እውነት ስንፈጥር ሆድ አምላካችን እንዲሆን ይሆን? ፈጣሪ የከፈተውንስ ሆድ ሳይዘጋ ያድራልን?
ሙዚቃው ቀጥሏል። ተው እንጂ ሆዴ ታገስ ሳጣም ቀን ስጠኝ ብሎ ይለምነዋል። ርህራሄ ለማያውቀው ሆድ አንጀት የሚበላ ልመና ምኑ ነው? ምንም። የሰውን በደል እና ክፋት በብልሃቴ ብርቅም አውጥቼ የማልጥለው ሆድ የተባለ ጠላት ግን ይዤ እዞራለው። ፈጣሪ የአለሙ ቢከብደኝም እንደው ከሞቴ በዃላ ያለውን ያስበኝ ብሎ በምድር ላይ ጠላቱ እንዳሸነፈው ያውጃል።
ከዚህ ሙዚቃ ለየት ያለ ሀሳብ የተነሳው የመጨረሻው ስንኝ ላይ ነው። በሞት የተለየኝን ዘመዴን ቀብሬ በአግባቡ ጮኼ ሳይወጣልኝ ሀዘኑ እንኳን ሳይረግብልኝ እርምክን አውጣ ተብዬ ዳግም አንተን እመግባለው ይላል። ሆድ ከሀዘን ሁላ በላይ ነው። አልቅሶ እንኳን ያልወጣለትን ሰው የእዝን እያልን ሆዱን እናባብለዋለን። 'ህይወት ይቀጥላል' ከሚለው አባባል በላይ ልብ ብለን ካየነው 'መብላት ይቀጥላል' የሚለው እውነትነት አለው። ህይወት ሊቀጥልም ላይቀጥልም ይችላል፤ ያው በቁም መሞትም ስላለ። ሆድን መቀለብ ግን እስከ ሞት ይቀጥላል።
ብቻ ምን ለማለት ነው ሽሮም በላ ክትፎ ተመስገን ብሎ ለማይዘጋ በር ብዙ አናንኳኳ ገርበብ አድርገን መተው ይልመድብን ለማለት ነው።