ተረት ተረት

1 min read
tarate-tarate

Let the pain come, stay and leave.

አንድ ለፍቶ አዳሪ ወዝ አደር ነበር። በህይወት እስካለ ድረስ ለፍቶ፣ ጥሮ እና ግሮ እንዲኖር ብቻ የተፈረደበት። በስራ ላይ እያለም እንደማንኛውም ስጋ ለባሽ አንዳንዴ ይጋጋጣል፣ ይፋፋቃል፣ አልፎ አልፎም ይደማል ከፍ ሲልም ይቆሰላል። ህይወቱ በእንቅፋት እና መሰናክል የተሞላ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ይህ ሰው ክፉኛ ተጎዳ፣ በጣም ተቆረጣ። ብዙ ደምም ፈሰሰው። ቀለል ላሉ ጉዳቶቹ እንደሚያደርገው ይሄን ቁስሉን በጨርቅ ጠቀለለው። ጥብቅም አደርጎ አሰረው። ያዩት ጓደኞቹም ተመላልሰው ጠየቁት አጽናኑት ከዛም ኑሮ ነውና ወደ ስራቸው ተመለሱ። ቁስለኛውም ምንም እንኳን ባይሻለውም ወደ ስራው ተመለሰ። እያደር ሲቆይም ይህ ቁስል አዲስ ስሜትን አመጣ። ብርድ ሲመጣ ንፋሱ ሲበረታ ይጠዘጥዘው ጀመር። ጸሃይ ሲወጣም መጥፎ ጠረን ማምጣት ጀምረ። መቸገሩን ያስተዋሉ ጓደኞቹም 'ቁስልህን እንይልህ' ብለው ጠየቁት። ለቅርብ ጓደኞቹም ጨርቁን ፈቶ አሳያቸው። ገና ገለጥ ሲያደርገውም ሽታው የከፋ፣ ለአይንም የሚቀፍ መግል ይዞ ተገኝ። ከመሃላቸውም ጥቂቶቹ ተሳለቁበት፣ በሚቀረናው ጠረንም ተጠየፉት። በዚህም የተሰማው ይህ ቁስለኛ በሌላ ጨርቅ መልሶ ጠፍንጎ አሰረው። ሁለተኛም ለሰው ላያሳይ ለራሱም ላያየው ቃል ገባ። ያ የመገለ ቁስል ግን አሁንም አልዳነም። ሽታው፣ ህመሙ አንዳንዴም ደሙ ጊዜ ና ወቅትን እየጠበቀ መታየቱን ቀጠለ፣ ህመሙን ለሰው እንዳይናገር የሚገባው የሚረዳው ያለ አልመስል አለው። ድንገት እንኳን የሚረዳው ከተገኘም ደካማ መስሎ መታየትን ፈራ። ከህመሙ ክብሩ በለጠብት።

ታዲያ አንዴ በስራ አጋጣሚ ከአንድ ዕድሜው ከገፋ ሰው ጋር ተዋወቀ። ይህ ሰው ከራስ ግንባሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በጠባሳ የተሸፈን ነበር። ከቀላል፣ ትኩር ብለው ካላዩት ብዙም ከማያስታውቅ ጠባሳ ጀምሮ እስከ ከባድ፣ ለአይን በሚያስጠሉ ና በሚቀፉ ጠባሳዎች የተሸፈነ ነበር። የተሸፈነም ሆነ የተጠቀለለ ቁስል ግን አልነበረውም። ያዩት አላፊ አግዳሚዎች በጠባሳ ተሸፍኖ በአደባባይ መታየቱን እንደ ድካም ቆጠሩት። ከኋላውም አወሩበት። የራሳቸውን ጒብዝና እያደነቁ ተደሰቱበት። ያ የተቸገረ ቁስለኛም ይሄን ሰው ቀርቦ ጠየቀው። " እንዴት ይህን መሰለህ በሰው ፊት መታየት አስቻለህ?" ሰውየውም መለሰ " ይህ ፊቴ ላይ ያለው ትልቁ ጠባሳ አንድ ትልቅ ዛፍ ስቆርጥ መጥረቢያው ተፈናጥሮ የቆረጠኝ ነው፣ ይህ እጄ ላይ ያለው ስፊት ደግሞ ድንጋይ ጠርቤ ሳስተካክል ወድቄ የተሰፋልኝ ነው፣ ያኛው ደግሞ የሰው ቅጥል ስሰበስብ ክፉ አውሬ ነክሶኝ የቀረ ጠባሳ ነው። ቢሆንም ሁሉም የኔ ነው።" የራሱ ቁስል አለመደርቅ ያሳሰበው ይህ ቁስለኛም " እንዴት እንዲ ደረቀልክ?" አለው። " ሁሉንም ቁስሎቼን በየጊዜው አጥባቸው ና አጸዳቸው ነበር። ህመሜንም በደንብ አስታምመው ነበር። እንደዛም ሆኖ አንዳንዱ ቁስል መልሶ ይመረቅዝ ነበር። እኔ ግን ተስፋ ሳልቆርጥ አክማቸው አንዳንዴም አሳክማቸው ነበር። " አለው በፈገግታ። " ሰውስ ምን ይላል?" አለ የሰማቸውን ሀሜት ና ቧልት አስታውሶ። ትልቁ ሰውዬም አለ " ይህ የምታየው ሁሉ ከእኔ የበለጠ አንዳንዴም ከእኔ ያነሰ ቁስል እና ጠባሳ አለው። እኔ ከእነሱ፣ እነሱም ከእኔ አይሻሉም። ሁላችንም የዚ አካባቢ ለፍቶ አዳሪዎች ነን።"

Comments (0)
No comments yet