ሰውየው ሰውየው ይምጣልኝ ሰውየው

1 min read
saweyawe-saweyawe-yemethaalenye-saweyawe

በጥቂት ቃላት ብዙ ለሚባልላቸው ፣ መገኛቸውን ለማናውቀው ፣ ለእነሱ።

ያየሁት ስብሰባ ላይ ነበር። አንድ ጸሃያማ የማይመች ቀን ላይ። ድንገት ዞር ስል ሲስቅ አየሁት። የሰው ልጅ ሲስቅ እንዲ እንደሚያምር ለምን እስከዛሬ አልተነገረኝም? የፈገግታ አስቀያሚ ባይኖረውም የእሱ ግን ከሰው ልጅ ፈገግታ በላይ ነው። ስቆ ዝም አለ። ለምን ይሆን ዝም ያለው? አስቴር አይንህ አይንህ ብላ ዘፍና ጥርስህ ጥርስህ........ፈገግታህ ፈገግታህ ለምን አላለችም? አጠገቤ አይመጣም? አሰብኩ በአንዴ ከፈገግታው እስከ አስቴር ከዛም አብሮኝ ሰለመቀመጡ አሰብኩ። አሰላሰልኩ።ተመኘው። ያው አልመጣም።

***************

አንድ ቢሄዱ ቢሄዱ የማይደረሰበት የሚመሰል በርግጥም ለመድረስ ዓመተ ዓለም ወደ ኋላ ለመቁጠር የሚያስመኝ የከተማዋ ጫፍ ልሄድ ነው። ስልኬ ና ጆሮዬ ላይ ደሞ አስቴር ነበረች። በይቅርታ ዘፈኗ "ሰውየው አለ ወይ-------የምነግረው አለኝ------አኔ መንገደኛ በሰማይ በራሪ በምድር ተሽከርካሪ-------ሌት ተቀን አንጎራጓሪ-----" የታክሲው የኋላ ወንበር ላይ በጥግ በኩል ነበር የተቀመጥኩት። ታክሲው አይሞላም እንዴ? መንገዱን ሳልጀምረው ሰልችቶኛል። " አህ በእመቤቴ ማርያም በጌታዬ እናት-------አህ ልቤን ከቦታዋ ከኔው መልሳት-----አህ እኔ መንገደኛ ፍቅሬን አልጨርሰው-----አህ ከይቅርታ ጋራ በል ልቤን መልሰው------ይቅርታ----" ስብሰባው ላይ ያየሁት ሰው ትዝ እለኝ። ይኖር ይሆን? የት አገኘው ይሆን? ተመኘው። ልቤን በፈገግታው ሲወስድ ፍቃድ አልጠየቀኝም። በውሃ ደራሽ ጥርግ ነበር ያልኩት። እኔም እንደ አስቴር 'ተገኘው' አልኩ።

****************

እዚ አሰልቺ ስብሰባ ላይ ከዛ ሰው ፈገግታ ውጪ አንድ የረባ ነገር የለም። ለምን መድረኩ ላይ ወጥቶ ለአንድ 10 ደቂቃ ፈገግ አይልልንም? ይሄን በማሰብ የሃሳቤን ምጡቅነት ሳደንቅ አልፎ አልፎም ለብቻዬ ፈገግ እያልኩ ስዝናና ሰውየው ብድግ አለ። እንዴ 'Law of manifestation'! መድረኩ ላይ ወቶ ሊስቅልኝ ይሆን? በዚ አያያዜማ አንድ 'How to make the cute guy you saw smile?' የሚል አጠር መጠን ያለች መጽሃፍ እጽፋለው። 'Rules and uses of positive attraction' ን በመጠቀም። ድምጽ ማጉያውን ያዘ። ሊዘፍን ይሆን? ጓጓው። የሆነች እራፊ ወረቀት አውጥቶ ማንበብ ጀመረ። እግዜኦ! ድምጹ እንዴት ያምራል? ይሄማ ቀልድ ነው። እንዴት አንድ ሰው ይሄ ሁሉ ነገር ይሰጠዋል? እኛስ?! እግዜር ምን እያሰብክ ነው? የድምጹ ነገር.............ማር በጆሮ እንደሚጥም ዛሬ አየሁ። አንኳን ተሰበሰብኩ አበባን የሚያስንቅ ፈገግታ፣ መኖርን የሚያስናፍቅ ድምጽ ከይት እሰማ ነበር? ደሞ እርጋታው! በእያንዳንዱ አረፍተ ነገር መሃል ስክን ያለ እረፍት ይወስዳል። ቀና ብሎ ታዳሚውን ያያል። ከዛም ዝቅ ብሎ ያነባል። ማን ይሆን ስሙ? ፈገግ አይልም? እጄን ላውጣ እና እስኪ የእዮብን አንዲት ዘፈን ዝፈንልኝ ልበለው? ተቁነጠነጥኩ።

*******************

'እናት ሂሳብ!' 'ሂሳብ እያለሽ ነው' አጠገቤ ያለችው ልጅ ነካ ነካ አደረገችኝ። ኡፍ በቃ እዚ ሀገር ደህና ትዝታን እንኳን ማጣጣም አይቻልም አይደል?! ብቻ መልሶ መሰብሰብ ያን የሰው ሙሉ ማየት አሰኘኝ። አይገርምም ለረጋፊ ጥርስ እና ለሚሻክር ድምጽ እንዲ መሆኔ? የሆነው ሆኖ የት ና ምን ይሆን መገኛው?

Comments (0)
No comments yet