ሳህሌ

1 min read
saahelee

ይድረስ የማይረሱ ለመሰላቸው ሰዎች እና የማያልፉ ለመሰላቸው ቀኖች

ቀን48

ሳህልዬ ዛሬም አልመጣም አልደወለም። አልናፍቀውም ይሆን? ረሳኝ ማለት ነው? በቃ የኔ ና የሱ ነገር እንዲህ ሆነ ማለት ነው? ሳህልዬ እኮ ግን ይወደኛል አሁን እንዴት ጨከነ? “ሜክሲኮ ሜክሲኮ እ ሜክሲኮ አለ?” ሀሳብ ሳይጨረሰኝ በፊት ወደ ታክሲው ልግባ። ያው ባዶ መንገድ ላይ ተገትሬ ሳህልዬን ከማሰብ ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ ብቀጥለው ይሻለኛል።አይ እኔ ይህ አሁን ፍቅር ነው በሽታ? ሳህልዬ እኮ ይሄኔ ሌላ ሴት ወዷል። ከኔ የበለጠች ቆንጆ አግኝቶ ይሆናል። እኔ ነኝ እንጂ መጋኛ እንደመታው ሰው ፈዝዤ የቀረሁት። አይይይ ግን በዚ ፍጥነት እኔን ረስቶ ሌላ ሴት ጋር አይሄድም መቼም።ረዳቱ ጥሪውን ጨርሶ ወደ ታክሲው ገባ። እንደሞላ እንኳን አላወኩም ነበር። ሳህልዬ በሃሳብ እያጫወተኝ ነው።

እዛው ቁጭ እንዳልኩ የአስቴር ዘፈን ተከፈተ።ታክሲ ውስጥ ዘፈን ሲከፈት ደስ ይለኛል፥ሳህሌ የሚወዳቸውን ሙዚቃዎች በአጋጣሚ ሲከፈቱ ልቤ ሙልት ይላል።ሳህልዬ እኮ ጥሩ የሙዚቃ ምርጫ አለው፥ያውም ጥቂቶች ብቻ ከተቸሩት አዳማጭ ጆሮ ጋር። "እስቲ ሮዛ አስቱካን ክፈቺልኝ" ይለኝ ነበር ደስ ያለው ቀን። አስቴር የቤታችን የፍቅር መለኪያ ናት። በእሷ መከፈት እና መዘጋት ውስጥ የኔ እና የሳህልዬን የፍቅር ከፍታ ና ዝቅታ መናገር ይቻላል።

"አይዞኝ አይዞኝ አረ አይዞኝ----" አስቴር ቀጠለች። ሳህልዬ ይሄን አሰምቶኝ አያውቅም። መጽናናት እንደሚያስፈልገኝ አውቆ ቀድሞ ምን አለበት ጋብዞኝ ቢሆን ኖሮ።

"ይመጣል ይሔዳል ፍቅር እና ሰው

ወስዶ ማይመልስ ያ ሞት ብቻ ነው

ሆዴ ረጋ ረጋ በል ረጋ ረጋ አትውረድ ቆላ አትውጣ ደጋ---"

ምን? ጮክ ብዬ ምንድን ነው ምትለው ብዬ ተሳፋሪውን ብጠይቅ ደስ ባለኝ። አስቴር ምን እያለች ነው? እንደዛ የሚወዳትን ሳህሌን እንደ ተራ ሰው ቆጥራ ነው ይመጣል ይሄዳል ፍቅር እና ሰው የምትለው? ድሮም እኮ--- "ወራጅ! አውረደኝ እዚ ጋር" የምን ሜክሲኮ ድረስ መሄድ ነው።

ቀን 75

ሳህሌ ዘለቀ አሁንም አልመጣም።

ቀን 105

አስቴር እውነቷን ነበር። የማይመጣ ሰው የማይሄድ ፍቅር የለም። በሄደበት የቀረው ሳህሌ ተብዬው ብቻ ነው።

ቀን 210

አስቴር እውነቷን ነው። የማይመጣ ፍቅር የማይሄድ ሰውም የለም። ሞት ስላልቀደመኝ ሳህሌም ተረስቷል።

 

Comments (0)
No comments yet