ሮዛ ሮዚና

1 min read
rozaa-rozinaa

እሷን ላየ፣ እሷን ላዳመጠ

" ብዙም ተወደጄ አላውቅም። እንዴት ብዬ ላስረዳህ? ይሄ መፈቀር፣ መደነቅ አለ አይደል ሴት ልጅ በቀላሉ የምታገኛቸው የስሜት ምግቦች ተሰጥተውኝም ቀርበውልኝ አያውቁም። ድሮ ድሮ እንደትልቅ ነገር አልቆጥረው ነበር። ብዙ አላማ፣ ብዙ ሃሳብ፣ ብዙ ነገዎች ነበሩኝ። አያስጨንቀኝም ነበር። ኋላ ላይ ከሰው ጋር በደንብ ስቀላቀል ሌሎችን ሳይ እነሱ ጋር ሞልቶ የተረፈው አብዛኛው ጋር ለምራጭ የቀረበው ይህ የማያቋርጥ ና የማያባራ የፍቅር እና የአትኩሮት ዝናብ እኔ ጋር እስከዚም እንደማያካፋ ተረዳሁ። ምን መሰለህ እኔ መምረጥ አልፈልግም። በቃ አለ አይደል አንድ ደህና ሰው ካለኝ ይበቃኛል። ብዙ አድናቂ አለኝ ብዬ በትዕቢት መሞላት አልፈልግም። እንጃ ራሴን አላምነውም፣ እንዲ አይነት ዕብሪት ወደ ልቤ ድርሽ እንዲል አልፈልግም። ግን ደግሞ አየህ ለእንደኔ አይነት በዚ ዓለም ላይ ያለውን ቦታ አጥብቆ ማወቅ ለሚሻ ሰው በሌላ ሰው ዐይን ውስጥ ምን አይነት ስፍራ እንዳለኝ ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር። አለም ያንቺ አይደለችም እንዳትለኝ። አውቃለው ዓለም የኔ እንዳልሆነች ግን ደግሞ እስካለሁባት ደረስ ትንሽም ብትሆን መቆያዬን ልታዘጋጅልኝ ይገባል። ብቻ ሀብዬ ከብዶኛል።" ትንፋሽ ሳትወስድ ነበር ይሄን ሁሉ ያወራቺኝ። ሃሳቧ ይገርመኛል፣ አንዳንዴም ያስቀኛል፣ አልፎ አልፎም ያናድደኛል። ብቻ ሀሳቧ ብዙ፣ ስሜቴም ብዙ ነው። አንድ ነገር እያወራች መልሱን እራሷ ትመልሳለች። መልሳ ደግሞ ሌላ ጥያቄ ትጠይቃለች። የራሷ ንግግር ላይ እንደምትጨምረኝ ይሰማኛል። ግን ያው ሁሉንም እወደዋለው።

 

 

"አሁን ለምን ወደ ጉዳይሽ አትገቢም ሮዚና" አልኳት ወሬውን ለመስማት ጓጉቼ።

 

 

"ባለፈው እንደውም መስሪያ ቤት ወረቀቱን ሊያስጨርስ የመጣው ልጅ ትዝ ይልሃል? ያ እንደውም እመቤት ቢሮ ሲመላለስ የነበረው?" አየቺኝ ልጁን እንዳስታውሰው ጓጉታ። " እ. . . ትዝ አለኝ መሰለኝ ያ እንደውም እንዳያየኝ ብለሽ ስትደበቂው የነብረው ልጅ ነው አይደል? ምን ሆነ?" እመቤት ቢሮ ከመመላለሱ ይልቅ በእሷ ድብብቆሽ ነበር ትዝ ያለኝ።

 

 

"ሀብዬ እኮ ለዚህ እኮ ነው ምወድህ ብዙ ነገር አትረሳም። ብቻ አዎ እሱ። እሱ ማለት የቀድሞ መስሪያ ቤቴ የማውቀው ልጅ ነው። ብቻ ምን መሰለህ ሀብዬ እንዳልኩክ ብዙም የፍቅር ነገር አይገባኝም። ሰዎች እንዴት እንዲ እንደሚፋቀሩ በጭንቅላቴ አስልቼ መረዳት ይከብደኛል። ያው ምናልባትም ፍቅር በጭንቅላት የሚሰላ ነገር ስላልሆነ ይሆናል። ብቻ እሱን ሳላስበው ወደድኩት ያው መውደድ እንደዛ ከሆነ ማለት ነው። ብዙ ነገሩ ያስደስተኝ ነበር። ዝምታው፣ ለስላሳ ድምጹ፣ ቁጥብ ፈገግታው ብቻ የሆነ ምናባዊ ሰው ነበር የሚታየኝ። በቃ እልፍ ሲል የሆነ አየር አብሮት እልፍ ይላል። ንፋስ ነው እንዳትለኝ ብቻ፣ ለስሜቱ ብዙም ቅርብ ስላልሆንኩ ይሆን እንጃ የተሰማኝን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል።" ሃሳብ እና ጭንቀት እንደጎበኟት ከፊቷ ላይ ማንበብ ቀላል ነበር። እውነት ሮዛ የፍቅርን ነገር በደንብ አታውቀው ይሆን?

 

 

" እና በቃ እሱን አልፈ፣ ቆመ ብዬ መከታተል ደሞዝ የማልቀበልበት ስራዬ አደረኩት። ሲስቅ አብሬው ስስቅ፣ ሲብሳጭ አብሬው ስቆጣ ብቻ ምንድን ነው ሚባለው አዎ ማይ ካፒቴን ሆነ። የስሜቴ መሪ በለው። እና ግን ሀብዬ የአይን ክፋቱ መርጦ አለማሳየቱ ነው። እኔ ተቀበልኩም አልተቀበልኩም ሁሉን ያሳየኛል። እንደዛ በስስት የምወደው ልጅ አንዷን የስራ ባልደረባዬን ወዶ አገኘሁት። እንዴት አወቅሽ እንዳትለኝ። ጎረቤት የተሰራውን ወጥ ለማወቅ የራስህን ቤት ድስት ማሽተት በቂ ነው። እኔ ቤት ያለውን ስሜት እሱ አይን ላይ ለማንበብ ቀናት አልፈጀብኝም። እኔ እሱን እሱን ሳይ እሱ እሷን እሷን።" እኚህን ቃላት ከአፏ ለማውጣት እንዴት እየተጣጣረች እንደነበር ገብቶኛል። ለማመን እና ለመቀበል የሚከብዱ ስሜቶች ናቸው። ይገባኛል።

 

 

" ሀብዬ በእውነት ከፍቶኝ ነበር። እንደው ባይወደኝ እንኳን ምናለ እሷን እፊቴ ባይወዳት? ዓለም ግን ለምን ይሆን እንዲ የከፋችው? እንዴት ለእንግዳ ያውም ቤት ግባ ላልተባለ ሰው ጓዳህን ታሳያለህ? እንዴት የማይኖርበትን ቤት አሳይተህ ትነሳዋለህ?" ዓለምን ነው ወይስ ልጁን ነው እየወቀሰች ያለችው?

 

 

"ምንም ብወደው ስላልወደደኝ ከፍቶኝ ነበር። እኔው ፊት ሌላ በመውደዱ ደግሞ ትንሽም ቢሆን እንድጠላው አደረገኝ ። ፍቅር ውስጥ ጥላቻም አለ ማለት ይሆን? እንጃ አላውቅም። የኔ ስሜት ይገባዋል ብዬ አላስብም፣ ሩቅ ነበርኩ። ግን ደግሞ ራሴን ምን ያህል ዝቅ እንዳደረኩ ሳስበው አፍራለው። አውቃለው ሀብዬ ፍቅር ዝቅ ማለት ነው ምናምን እንደምትለኝ ግን ደግሞ እኔ ፍቅርን አላውቀውም። እኔ ጋር እንኳን ዝቅ ብሎ ደረቱን እንኳን ነፍቶ መጥቶ አያውቅም። ብቻ ግን ሀብዬ ለእንደኔ አይነቷ የውሃን ለብታ በቅጡ ለይታ ለማታውቅ ሴት በሙቅ ውሃ መላጥ ተገቢ ነው ትላልህ? እኔ አይመስለኝም።" አይ ሮዛ ይህ ማለቂያ የሌለው ጥያቄዋ የቱ ጋ ይሆን የሚያርፈው? የትስ ይሆን መልስ የሚያገኘው?

 

 

"ሀብዬ ግን እውነት እኔ ለመወደድ አልበቃም እንዴ? ሳትዋሽ ንገረኝ እ. . . እኔ እኮ አልቀየምክም። ደሞም አይከፋኝም። ምኔ ነው የሚደብረው? ለምን ይሆን ፍቅር እንዲ የሸሸኝ? ሀብ እስኪ ንገረኝ?" ስለሮዛ ግልጽነት እና የጠያቂነት ልክፍት በደንብ አውቃለው። ዛሬ ስታወራኝ የገባኝ ግን እውነትም ሮዛ ፍቅርን አለማወቋ ነው። የጎረቤት ወጥ. . . ነበር ያለችው አይደል ታዲያ ሮዛ ያን አይነት ስሜት መረዳት ከቻለች እንዴት የእኔን ዐይን ማንበብ አቃታት? 

Comments (0)
No comments yet