ቃ. . . ል

1 min read
qaa-le

በመጀመሪያም ቃል ነበር. . .

ራሴን መልኬን አየሁት።  ትናንት የት ነበርኩ? ዛሬ የት ነኝ? ያኔ ማን ነበርኩ አሁንስ ማን ነኝ?

ከ 2 አመት በፊት. . .

አዋሪኝ ለምን ዝም ትያለሽ?

እሺ

እኮ አውሪያ

እሺ

ሳህሌ እባላለው እእእእ ለማቆላመጥ አይመችም ማን ትይኛለሽ?

ይከብዳል ለማቆላመጥ አይደል. . . ሳህሌ ይሁና በቃ

እሺ ሳህሌ ይሁን አንቺን ማን ልበል?

ሮዛ. . . ሮዛ እባላለው

ሮዚ እልሻለው በቃ

ከ 3 ወር በኋላ

'ሮዚዬ አንቺ እኮ የሚመስልሽ የለም። ሰው እንዴት ከሁሉ ይታደላል? ታውቂያለሽ አንቺ ስለእኔ የምታስቢው ነገር ያሳስበኛል አለ አይደል ስለእኔ ምን ታስብ ይሆን ምን ትል ይሆን ብዬ አስባለው። ' እንደመሽኮረመም አለ። 'ማይ ኢምፕረሽን ጥሩ እንዲሆን ነው ምፈልገው። ስለእኔ ጥሩ እንድታስቢ ምናምን' ፈገግ አለ።

ሳህሌ ይጨነቃል። መጨነቅ መልካም ነው።

ከ 6 ወር በኋላ

'ሮዚዬ አንቺ እኮ ቤተሰቤ ነሽ። አለ አይደል በምንም የማልተካሽ በማንም የማልለውጥሽ። አንቺን የሚመስል የለም እኮ. . .'

እኔ ቃላት አይደልሉኝም ቤተሰቡ ብሆንም ባልሆንም ያው ሳህሌን እወደዋለው። ሳህሌ የሚቆይ ይመስላል።

ከ 1 አመት በኋላ

'ሮዛዬ ሰው ባልነበረበት ጊዜ ሰው የሆንሽልኝ. . .ከስንቱ እንዳተረፍሺኝ ታውቂያለሽ።  ሮዛዬ አንቺ እኮ አምሳያ የለሽም።'

ሳህሌ ጥሩ ቃላት ይጠቀማል። ምን ማለት እንዳለበት ያውቃል። እኔ ለቃላት ብዙም ነኝ።  ግን ደስ ይለኛል ሰው በመሆኔ ያውም ለሳህሌ።

ከ 6 ወር በፊት

'ሮዚ አልተግባባንም። እኔ አሁንም ቤተሰብነትሽን አልጠላሁትም። ጥሩ ነገር ነው ያለኝ ላንቺ። ግን ደሞ በቃ አለ አይደል ህይወት ውስጥ እንዲ ያለ ነገር ያጋጥማል። በሰላም ሳይቃቃሩ መለያየት ብሎም መጠያየቅ ይቻላል። ሮዛ ለመረዳት ሞክሪ'

ሳህሌ አልገባኝም። ምን ሆኖ ይሆን? የመረዳት አቅሜ ዝቅ ብሎ ይሆን?

ከ 2 ወር በፊት

'ሳህሌ ምን ማለትህ ነው? አልገባኝም ደነዝ አይደለሁም አስረዳኝ?' 

'ሄሎ ሳህሌ! መልስልኝ እንጂ ምን ማለት ነው ላገባ ነው ማለት ? እእእእእ ሳህሌ?. . . '

ዛሬ

ትናንት ማንም አይበግረኝም ነበር፣ የሳህሌ ንግግር ቢሆን እንኳ። ብዙ ብዙ አልፌ ነበር። ግን አንድ ቃል ብቻ ቀርታለች። 'አምሳያ የለሽም ፣ የሚመስልሽ የለም. . . አምሳያ. . . ምትክ. . . ምስል።' እኔ እኮ አምሳያም ምትክም አልነበረኝም። ለሳህሌ ደም የለኝምም።

ትናንት ቃል የማይደልለኝ፣ ሙገሳ የማያስደነግጠኝ፣ ፍቅር የገዛኝ ሰው ነበርኩ። ዛሬ ቃላት የምፈራ፣ የፍቅር ስሩ ቃል መሆኑን የማውቅ፣ የማልደመም ነጻ ሰው ነኝ።

Comments (0)
No comments yet