ነጭ ነጥብ

1 min read
nache-nathebe

ውበት ሀሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው እዲል መጽሃፉ

መልኬን መስታወት ላይ አየዋለው። የተለመደ ድርጊት አልነበረም። ፊትን በመስታወት አተኩሮ እንደማየት አሰልቺ ነገር የለም። ያው ለኔ። አሁን ግን ገጽታዬ ላይ ለውጥ አለ። ዕድሜ ከሚወሰደው የልጅነት ወዜ በተጨማሪ ሌላ አዲስ ሰፋ ያለ ለውጥ ይታየኛል። ጸጉሬ ላይ ረጃጅም ነጫጭ ጸጉሮች በዝተዋል። ከጥቂት ግዜ በፊት በጣት የሚቆጠሩት ነጫጭ የጸጉር ዘንጎች አሁን ላይ ከግንባሬ ጸጉር አንስቶ እስከ ውስጥ የጸጉሬ ክፍል በምቾት እያደጉ ነው። ሳላረጅ እየሸበትኩ ነው። ፊቴን ፍጥጥ ብዬም ሳየው አፍንጫዬ ላይ ነጭ ነጥብ ይታየኛል። በምናቤ ፈጥሬው ይሆን ብዬ የሰላሳ ደቂቃ ዕረፍት እየወሰደኩ ደጋግሜ አይቸዋለው። ግን ነበር፣ ትንጥዬ ብዙም ደምቆ የማይታይ ነጭ ነጥብ።

ልጅ እያለው ጆሮዬ አካባቢ ነጭ ጸጉር ነበረቺኝ። ያይዋት መምህሮቼ 'አሮጊቴ' ይሉኝ ነበር። ከፍቶኝ አያውቅም። ነጩ ጸጉሬ መለያ ምልክቴ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። በኋላ ላይ ምንም ጥቅም የላትም ተብላ በግድ ተነቀለች። ከዛ ይህቺ ሽበቴ ዩንቨርሲቲ ስገባ አምራ እና ደምቃ ብሎም ቆድዬን አንጥታ መጣች። ያው እንደ ከተማ ሰውነቴ መታየት፣ መታከም አለብኝ ብዬ ሆስፒታል ሄድኩ። እዛም ሰማሁ፣ ተረዳሁ፣ እስኪ እጆችሽን ዘርጊ ተባልኩ፣ ታየው። በሰዓቱ ሌላ ቦታ አልወጣብኝም ነበር። የሆነች ቅባት ይዤ ተመለስኩ። ከዛ በኋላ አልፎ አልፎ በመስታወት ፊቴን ከተቻለም ጸጉሬን መመልከት ጀመርኩ። ነጩን ምልክቴን ፍለጋ።

ሰዎች ሰለእኔ እና ለምጽ ምን ያስቡ ይሆን ብዬ በአጋጣሚም ቢሆን ሃሳቡን አነሳለው። ያው የሁሉም ሰው ፊት ላይ የሀዘኔታ እና 'ምስኪን' የሚሉ አጠር ያሉ ማጽናኛ ገጾችን አነባለው። አንዴ ለአንዱ ወዳጄም " መቼም ቆዳዪ ቢነጣም ታገባኛለክ አይደል? " አልኩት። የሳቀው አንድ አንቀጽ የሚሞላ አጠር ብሎ ግን ብዙ መልዕክት ያለው ሳቅ አሁንም ትዝ ይለኛል። 'ተይ እንጂ! አንቺ ማን ሰለሆንሽ?' የሚል እውነት ቀመስ መልዕክት ነበረው ሲጠቃለል። ስቄ አለፍኩት። ቆይቼ ሳስበውም ምን ያህል እንደሚከብድ ተረዳሁት። አልተቀየምኩትም። ብቻ ከሰዎች ቦርቀቅ ያሉ በርቺ አዘል መልዕክቶች ተቀብያለው። እኔስ ምን አስባለው?

እኔ ምን አስባለው? ብዙ ነገር። ምናለብት እንደ አለምዓየሁ ገላጋይ ዕድሜዬ ገፋ ሲል ብቻ መስፋት ቢጀምር? ያው እሱንም መስፋት ካስፈለገው። በዚ ብልጭልጭ ዓለም ውስጥ በቆዳዪ ንጣት የሚዥጎረጎረው መልኬ ቦታ ይሰጠው ይሆን? እንደው የበሽተኛ ኑዛዜ አይሁንብኝና ቆዳዬ ቢነጣም ባይነጣም የመልክ እና ቁንጅና የተጋነነ ዋጋ አይገባኝም። ማንም ሰው ቤተሰቡን ና መልኩን መርጦ አይወለድም። በምድር ያለ ሰው ግን ሰውን ለመውደድ እንኳ አንዳንዴ የቤተሰቡን ማንነት አይቶ ና መርምሮ በአብዛኛውም የሚፈልገውን፣ የሚማርከውን መልክ አስልቶ ና አማርጦ ልቡን ይከፍታል። ሰው መርጦ ና ፈቅዶ ከሚያሳየው ባህርይ እና ከሚኖረው የህይወት ዘይቤ ይልቅ ጠፍጥፎ ያልሰራው የሚያረጀው ቁንጅናው ቦታ ይሰጠዋል። የሆነው ሆኖ ግን አገባ ይሆን? አግብቼስ እወልድ ይሆን?ልጆቼም እንደኔ ይሆኑ ይሆን? ቆዳዬ በሙሉ ሲነጣ እገለል ይሆን? ይሄን ሁሉ እጠይቃለው። ግና ለምጽ ባይኖርብኝም እኮ እኚህን ነገሮች ላጣ እችላለው። የህይወትን መንገድ ማን ያውቃል? ዳሩ እኔም በውበት አለም ውስጥ ተፈጥሬ መልክን የሁሉ ነገር መነሻ እና መድረሻ ማድረጌ ነበር። ከምን ላይ ተገኝቼ ምን ልሆን?። ድሮ በእርግማን ነው የሚመጣው ሲባል እሰማ ነበር። የእውነት ተረግሜ ይሆን? ትዝ የሚለኝ አንድ ሁለቴ 'የተረገምሽ!' እና 'ይቀመጥልሽ' እንደተባልኩ ነው። ከልባቸው ይሁን አይሁን አላውቅም። ግን ከልባችው ቢሆንስ ሰውነቴ ላይ ይሆን እንዴ የሚቀመጠው? ለውጥም መፍትሔም ባይኖረውም አስባልው።

ግን ያ አፍንጫዬ ጠርዝ ላይ የወጣው መለያ ነጥቤን አየዋለው። ይሰፋ ይሆን? ምን ልመስል ይሆን?

Comments (0)
No comments yet