ሃሳበ ፍቅር
". . . ተራሮችንም እስካፈርስ ደረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።"
" ይረገም የሚለውን የሙሉቀንን ዘፈን ታውቂዋለሽ?"
" መሰለኝ ለያይኔ ነው ምናምን የዘፈነው ነው አይደል?"
" አዎ ግን ያው እኔ የምሰማው የራሴን ያይኔ እያሰብኩ ነው። እሷን ነው ማስበው።" ሃሳብ ይዞኝ ሄደ።
"ጅል እና ወረቀት የያዘውን አይለቅም የሚለውን አባባል ተፌ እና ሙዚቃ የሚሉትን አያውቁም፣ ከያዙም አይለቁም። ብለን ብንቀይረውስ?" ከት ብላ ሳቀች። ኑሮዬ የሚያዝናናው አንድ ሰው ተገኘ። እሷ ባትስቅብኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር?
" ቀልጂ አንቺ 'አያርገው እንጂ አቤት ሲደርስ፣ በሰው የሳቁት ሲሆን በራስ' ሲባል አልሰማሽም? አንዴ እስኪጠልፍሽ እኮ ነው።" በልቤ የኔን ቀን አይስጣት ብዬ ተውኘው። ቢሆን ቢሆን ጥሩ ላይ ይጣላት።
"ውይ ተፌ አሁን ደሞ ምን አደረክ? ምን አለችህ? ቆይ አንተ ለምን አርፈክ አትቀመጥም?" መቼ ይሆን የኔ ትዕግስት የሚያልቀው፣ መቼ ይሆን የኔ ጉልበት የሚደርቀው?
"ትናንትና ትንሽ ደብሮኝ ከፍቶኝ ነበር። ከዛ በቃ እሷን ላገኛት ብዬ አሰብኩ።"
"እና ሄድክ?" ጩኸቷ ከቢሮ ውጪ ይሰማል። ለምን የመስሪያ ቤቱን ሰው ሁሉ አትሰበስቢውም?
"ለምን ሁላቸውንም በስማቸው አትጠሪያቸውም። ኑ ስሙልኝ ነው? ቀስ በይ እስቲ!" ይህን የተንቦረቀቀ ድምጿን ካልተቆጣጠረችው ያው የሰሞነኛ የቡና ቁርስ መሆኔ ነው።
"እኔ እኮ ግርም ነው ምትለኝ ምኑ ጅል ነህ በፈጣሪ ወልደው ቁጭ እንዳደረጉ ነው እንዴ ያለኸው? ሌላው ሁሉ ይቅር አንተ ቆይ ለራስህ ክብር የለህም? ቱ!" ትንሽ ለመንሾካሸክ ሞክራ ያው ቱ! የምትለው እርግማን ጋር ከቁጥጥሯ ውጪ ሆነ መሰል ያው እንደተለመደው ጮኸች። ያው እችለዋለው።
"ለማንኛውም ገና የሆነውን ሳትሰሚ አትንጣጪ ብቻ ቤቷ ሄድኩ እና ትንሽ ለማውራት ምናምን ሞከርኩ። ያው ምንም የተለወጠ ነገር የለም፣ ባልሄድ ይሻለኝ ነበር።"
"ምን አለችህ እንደው አንተ ውሻ!" እሷ ትላንት ካለችኝ የእሙዬ ስድብ በስንት ጣዕሙ
"ትንሽ ለማውራት ሞክሬ ነበር ግን በቃ ስራ ይዛ ነበር እና ትንሽ ደበረኝ። አረ አውሪኝ እንጂ ከፍቶኛል እያልኩሽ ስላት 'እና እኔ የድብርት ማራገፊያ ነኝ ወይስ የከፋው ሰው ማዝናኛ ማዕከል፣ ምን እንዳደርግልህ ነው ምትፈልገው?' አለችኝ። ያው እውነቷን. . ."
"ቱ ምን አልክ አንተ! እግዚኦ! አንተ በቃ መጨረሻህ ይህ ይሆን? ምን?!" አፏን ልይዛት ምንም አልቀረኝም በዚ አያያዟ እንኳን ቢሮ አካባቢ ያሉት ጥበቃውም ሰምቶ መምጣቱ አይቀርም።
"እስኪ ቀስ ብለሽ ጩሂ! አጠገብሽ አይደለው እንዴ ነው ወይስ የጊቢው ሰው ይወቅልኝ ነው?"
"አረ ይሄንንማ እንኳን የጊቢው ሰው የሞቱት ዘመዶችህም መስማት አለባቸው። አንተ የሞትክ ጓደኛ የለህም ይህቺ የሰው ስባሪ ሬድዮክ ነኝ ወይ እስክትልህ ደረስ እየሄድክ የምትርመጠመጠው? ሰሚ አጣህ? እሰይ ይበልህ! ድሮም ክብር አይወድልህም መከበር የጠላብህ ስለሆንክ በርታ!" አይ እሙዬ ለዚህች እንዲህ የሆነች ሌላ ሌላውን ብነግራትማ ምን ትል ይሆን?
"አሁን እሷም ሰው ሆና! ተው ተፌ ለሰውነት የማትበቃ አንዲት ቀፎ ላይ ሙክክ አትበል ተው ግን ተው!" አሁን ደግሞ ድምጿ ወደ ልመና ተቀየረ። ልብ ሰው ባለው ቢመራ ኖሮ ከእሙዬ በፊት የእሷንም የእኔንም ድምጽ ሰምቶ ለእውነት በፈረደ ነበር።
"እሙዬ ኣንደዛ ስትል መጀመሪያ ላይ ከፍቶኝ ነበር። በጣም ነበር የተሰማኝ። አንድ ቀን፣ በህይወት አጋጣሚ አንዴ አዋሪኝ ብላት ቦታዬን በግልጽ አሳየቺኝ። ሳስበው ግን ይሁንላት አልኩ ትሁንበት።" ያው ጩከት እየጠበኩ ነው። ዛሬ እሙዬ ታዋርደኛለች።
"አረ ባክህ! ነው እንዴ? አንተ ሰውዬ ዛሬ ምን ነካህ? ምነው ካለእኔ የፍቅር ዘብ የለም የክርስቶስ ግማጅ ነኝ አልክ? ሰው ስለመውደድ ሲያስተምሩክ ራስን ስለመውደድ ቆርጠው ጥለውት ነው? ወገኛ ነህ ባክህ! ምን ራስህን ብትጠላ ነው ሂድልኝ አትጠቅመኝም መዝናኛህን ፈልግ እያለችህ አይ እኔ ስለምወዳት ተመልሼ እሄዳለው ምትለው? ቱ አፈር ብላ!" ንዴቷ እየጨመረ መጣ። ያ መከረኛ ድምጿን ከሰበሰበችልኝ በቂ ነው።
"እሙዬ የምትይው እኮ ገብቶኛል ግን ምን መሰለሽ ፍቅር እና ክብር ሩቅ ለሩቅ ናቸው። አምላክም መንበሩን ትቶ ነው ለፍቅር የተሰቀለው። ክብሬ፣ ስሜ፣ ማቄ ካልኩማ ምኑን ፍቅር ሆነ? ያው እኔም እስኪያልፍልኝ እሷንም እስካልፋት መውደድ እንጂ ለምን እኮፈሳለው?"
"ተፌ ተፌ አልገባህም። አሁን በዚች ደቂቃ እንኳን እኔ ላንተ እንዴት እያፈርኩ እና እየተሸማቀኩ እንደሆነ ብታውቅ። ኡፍፍፍ. . . . እንደው እንዲ መናቅ እንዴት ይሆን የሚያስችልህ? ትንሽም ብትሆን እኮ ኢጎ ጥሩ ነገር ነው ተፌ።" እሙዬ ብዙ ስሜቶችን እያስተናገደች ነው። ቁጣ፣ ንዴት፣ ሀዘኔታ ከዛ ልመና አልፎ ተርፎም አፍረት
"ተፌ ሁሉም ይሁን እሺ ያለ ክብር ውደድ፣ ያለ ኢጎህም ተንቀሳቀስ ግን ቢያንስ ምን አለበት ለእሷ ይሄን ባታሳያት? ለራስህም መያዝ እኮ አንድ ብልሃት ነው" እኔ ላልጨነቀኝ እሷ ተጠበበች።
"አዎ ምን አልባት ለእሷ ማሳየት አይጠበቅብኝም። ያው ፍቅር አፕሩቫል ወይ ደሞ የማንንም ቫሊዴሽን አይጠይቅም። ግን በቃ ሰው ነኝ እና ንቃኝም ቢሆን የእሷን ትኩረት ማግኘት ያስደስተኛል። ከዜሮ ኔጌቲቭ ይሻለኛል። ያው ይህ የኔ ድክመት ሊሆን ይችላል። ተናዳም ቢሆን ብታየኝ እመርጣለው ጭራሽ ከማታየኝ፣ ከምትረሳኝ ያ የምትንቀው ልጅ ብሆን አይሻልም?።"
"እንጃ እንጃልህ የራስህ ጉዳይ ቆይ አንተ ፍቅርን ነው እሷን ነው የወደድከው?" ለእኔ አሁን ላይ ፍቅር ማለት እሷ፣ እሷ ማለት ፍቅር ናት ምንም ልዪነት የለውም። ለአሁን የሚሰማኝ ይህ ነው። ግን ማን ያውቃል ነገ ደግሞ ከእሷ ይልቅ የወደድኩት ሃሳበ ፍቅርን ነበር ብዬ አምን ይሆናል።