እኛ ጀብደኞቹ
ከስዕሉ ጀርባ ሁሌም ባዶ ጨርቅ አለ።
ዛሬ ቀኑ ሐሙስ ነው። ምን ያህል ስጠብቀው የነበረ ቀን እንደሆነ ሳስበው የእውነት የደረሰ አይመስለኝም። ህይወቴን ባልጠበኩት መንገድ የቀየረችውን ሴት የማገኘው ዛሬ ነው። የእሷ የስዕል አውደርይ የሚታይበት ቀን ነው። መንበረ ትባላለች። አሁን ላይ በጣም ታዋቂ ሰዓሊ ናት። ሰለእሷ የነገረኝ አንድ ጓደኛዬ ነበር። መንበረ ፊዚክስ ልታጠና ዩንቨርሲቲ ከገባች በኋላ የህይወት ጥሪዬ ሰዓሊ መሆን ነው ብላ ልትመረቅ ጥቂት ግዜ ሲቀራት አቋርጣ እንደወጣች ተረከልኝ። "አሁን አስቢው መንበረ በፊዚክስ ተመርቃ ቢሆን ኖሮ ፊዚዚስቷ ና ሰዓሊዋ መንበረ ትባል ነበር። በዛ ላይ የሰዓሊ ህይወት እንደምታውቂው ነው። ወይ ብር የለው ወይ ክብር የለው እንዲሁ ቀለም ስታጨማልቂ መኖር ነው። ቢያንስ ግን ያንን ብትጨርሰው ኖሮ ስዕሉን እንደመዝናኛንት እየሳለች ኑሮዋን ደሞ በትምህርቱ መግፋት ትችል ነበር።" ይሄን ሲለኝ ደራሲው ፓውሎ ነበር ትዝ ያለኝ "እኔ ደራሲ እንጂ ኢንጂነር እና ደራሲ መሆን አልፍልግም።" ብሎ ለእናቱ በአንድ ወቅት መልሶላት ነበር። መንበረም ያንን መልስ ለአንድ ሰው እንደመለሰች አሰብኩ። " እኔ ሰዓሊ እንጂ ፊዚዚስት እና ሰዓሊ መሆን አልፈልግም።"
ከዛች ዕለት በኋላ ህይወቴን በተለየ አቅጣጫ ማየት ጀመርኩ። እኔም እኮ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ነው መሆን የምፈልገው ለምንድን ነው የሂሳብ ባለሙያ ለመሆን የምማረው? ብዙ ጠየኩ ብዙ አሰብኩ ግን መልስ አጣው። እናም እኔም መንበረን ልከተላት ወሰንኩ መንበረን መሰልኩ። ትምህርቴን አቋርጬ ሙዚቃ ት/ቤት ለመግባት ወሰንኩ። ያው ጀብደኛም አይደለው። እናም ዛሬ የመንበረ ስዕሎች ለእይታ ይበቃሉ። እኔም ከስዕሎቿ በላይ መንበረን ለማየት በጣም ጓጉቻለው። ሳያት እንዴት እንደምስቅ፣እንዴት እንደማደንቃት፣ምን ብዬ ስለራሴ እንደምነግራት ሁሉ አስቤበታለው። መንበረ አርኣያዬም ብቻ ሳትሆን በአካል እስከዛሬ ድረስ አይቻት የማላውቃት ነገር ግን የምናብ መሪዬም ጭምር ናት። ይሄን ሁሉ ዛሬ ለመንበረ እነግራታለው።
ከብዙ ቆይታ በኋላ በመጨረሻም መንበረን አግኝቼ ለማውራት በቃው። እንዳሰብኩትም ፊቴ በሙሉ ጥርስ በጥርስ እስኪሆን በደስታ አድናቆቴን ገለጽኩላት። ብዙም ውዳሴ አትወደም መሰል ቀለል አድርጋ ብቻ አመሰገነቺኝ። እኔም ስለራሴ ማውራት ጀመርኩ። ከላይ ከላይ ስታይ በጣም ቁጥብ እና ትሁት ብመስልም በውስጤ የጀብደኝነት ትዕቢት እንዳል ግን በእያንዳንዱ ቃላቶቼ መሃል ፍንትው ብለው ይታያሉ። እኔ እኮ ህልሜን ለመከትል ስል የምማረውን ትምህርት አቋርጬ ሙዚቅኛ ለመሆን የወሰንኩ ሰው ነኝ። ልክ አንደ መንበረ.......
ለመንበረ ሙዚቃ ት/ቤት ለመግባት የምከፍለውን መስዋዕትነት፣ያንን ለማሳካት የምሄደበትን ርቀት እና ምን ያህል እንደምደክም በወፍ በረር ትንፋሽ ሳልወስድ አነበነብኩባት። እሷም አላሳፈረቺኝም በትዕግስት አዳመጠችኝ። እኔም እንደጨረስኩ ከመንበረ የመግረም እና የአድናቆት ቃላት መጠበቅ ጀመርኩ።በመንበረ መደነቅ ምን ያህል መታደል እንደሆነ እያሰብኩ ጀብደኝነቴ በመንበረ ትንፋሽ እስኪታወጅልኝ ጓጓው።ነገር ግን መንበረ ፊት ላይ በሃሳብ መዋጥ እና ዝምታን እንጂ የጠበኩትን አይነት የመደነቅ ስሜት አጣሁባት። መንበረን ምን ነካት?
"ውሳኔሽን አደንቃለው ታታሪነትሽንም ጭምር። ነገር ግን በንግግርሽ መሃል የእኔን ፈለግ እንደተከተልሽ ስታወሪ የሰማሁሽ መሰለኝ አይደል?" አለቺኝ። እኔም አዎ ብዬ አንገቴን ነቀነኩላት። ትንሽ ፈገግታ የሚመስል ብልጭታ ፊቷ ላይ አየሁባት።"ፍላጎትሽን መከተልሽ ጥሩ ውሳኔ እንደሆነ አምናለው። ቢሆንም ግን እኔ ያንን ውሳኔ ስወስን በህይወቴ ምን እንዳሳለፍኩ ምን እንዳጣው ታውቂያለሽ?" አለቺኝ። እኔም በውሳኔዬ ምን ያህል እንደጸናው ለማሳየት ተጨማሪ ማብራሪያ ቀጠልኩ።"ያው የሰው ልጅ የሚፈልገውን ለማሳካት ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚጠበቅበት እና በጉዞውም ብዙ ነገር እንደሚያጣ ግልጽ ነው። በዛ ላይ ህልምን ከማሳካት በላይ ምን አለ?" አሁን መቼም መንበረ ታደንቀኛለች ብዬ አሰብኩ። "ከህልም በላይማ አንቺ አለሽ። ይሄውልሽ ጀብደኝነት ጥሩ ነው። ያኮራል ያስደስታል። ነገር ግን ከዚ ሁሉ የሚታየው አሸናፊነት ጀርባ ያለውን ህመም እና መታወክ መገንዘብ አለብሽ።እኔ የዛኔ ትምህርቴን ሳቋርጥ ለወራት እንቅልፍ መተኛት አቅቶኝ ነበር። በማያቋርጥ ድካም እና ዝለት ውስጥ ለረጅም ግዜ ቆይቻለው። እናም ሁሌም ራሴን እጠይቅ ነበር ይሄ ሁሉ ለዚች አጭር ህይወት ተገቢ ይሆን? ያወጣሁት እና እውነት ይህቺ ዓለም የምትሰጠኝ ይመጣጠን ይሆን?"
በህይወቴ እንደዛሬው ጠብቄው ያልጠበኩትን ምላሽ ያገኘሁበት ቀን የለም።"ታዲያ ይህ አይደለም እንዴ የጉዞው አካል? ማለት አንድ ነገር ለማግኘት ብዙ ነገር ማጣት የለብንም?" መልስ ባሳጣኋት ብዬ ተምኘው።"ትክክል ነሽ እኮ ግን ደግሞ ተሳስተሻልም እያልኩሽ ነው። ምን መሰለሽ ዋናው ነጥብ፣ መሆን ያለበት ነገር በሙሉ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም። ስለተዋጋሽ ያሸነፍሻቸው የሚምስለሽ ጦርነቶች ምናልባትም ባትዋጊያቸውም እና በዝምታ ብታልፊያቸውም ልታሸንፊ የምትቺያቸው ሊሆኑ ይችሉ ነበር።ለጦረኛ የሚታየው ሰይፍ መምዘዝ ብቻ ነው። እንዲሁ ለሚጓዝ ሰው ግን የመንገዱ ሁኔታ እና የእሱ የወቅቱ ስሜት ነው ትርጉም የሚሰጠው።ማሸነፍ በትግል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በእርጋታ በመጓዝ ውስጥም ይገኛል እያልኩሽ ነው።" ይሄን ተናግራ ገና እንደጨረሰች አንድ ትልቅ ሰው ጠርተዋት ቻውም ሳትለኝ ሄደች።በውስጤ የነበሩት ጥያቄዎችም መልስ ሳያገኙ ወደ ቤቴ ተመለስኩ።እውነት ህይወት ከማሸነፍ በላይ ትርጉም ይኖራት ይሆን?