በሚስጥር ቅበረኝ

1 min read
bamisethere-qebaranye

ግርማ ወልደሚካኤል ፡ በምስጢር ቅበሪኝ (ሙሉቀን መለሰ) Girma Wolde Michael : Bemistir Kiberign (Muluken Melesse)

ለሰው ሁሉ ታማኛለህ አሉ. . .

" እሷ ቅናቷ አያስቀምጥ ምንም በጎ የላት"  ትለኛለህ አሉ።  "ሴት እንኳ ሰላም ካልኩ ጨርቋን ትጥላለች፣ ባንዲራ ምላሷን ታውለበልባለች፣ በዛ ጠንጋራ አይኗ ትገላመጣለች፣ እንቅልፌን ጠራርጋ ከነዘር ማንዘሩ ታባርረዋለች።"   

"ይሄም ይሁን ብላት መኖሬ ይከብዳታል፣ መሳቄ ይቀፋታል። እንደውም ባልፈው ' የአንተን ነገር ትቼ ኑሮ ልጀምር ነው። አሁን አሁን ሳይህ ሰውም አትመስለኝም፣ ሰው እንዳደረኩህ፣ አውርጄ እና አፍርሼ እሰርዝሃለው፣ ከሰው ማማነትም አስወግጄሃለው። ደግሞም እንዳትመጣ፣ ብትመጣም ሄጃለው፣ እኔ እንደው ትቻለው።' ብላ ጥላ ሄደች። ቆይ እኔ አሁን ሰውስ አይደለሁም? የምወርድ የምፈርስ ጎዶሎስ ኖሪያለው? መሄዱንስ ትሂድ አትምጣ እንደውም፣ ካለሷ ያለሷ ኑሮውም ውሃውም ተመችቶኝ አለው። ቸሩ መድሃኒዓለም በዕለተ ቀኑ ሰብስቦ ይያዝልኝ፣ ያን ጃዝ ምላሷን ቀርቅሮ ያስቀርልኝ።" እያልከኝ ነው አሉ።

ባይገርምህ ወሬ እኮ ይደርሰኛል፣ ያንንም ይሄንም እቀራርማለው። ነግቶለትስ ይሆን? አስታውሶኝስ ነበር? ብዬ እጠይቃለው። ልቤን እንደቀላል እንደቀልድ ብታየውእኔ እንደው አልተውኩም። ደህና አሳድረው፣ አልጋው አይጎርብጠው፣ ዝናቡም ይዝለለው ብዬ እሳላለው። ህሊናህ ሳያስብ ልቤን ብታስከፋው ፣ እኔ እንደው ነበርኩኝ ከተውክበት ቦታ። ብቀናም ወድጄህ፣ ብሳደብ ሳስቼህ፣ ግልምጫውም ፍቅሬ ሽልማቴ ነበር። ጠንጋራ ያልከው ዓይን፣ ያኔ በአንድ ወቅት 'ክብልል ያለ ኮከብ የእንቁ ፍንጣቂ የብርሃን ብይ ነው' ብለህ ትሳለመው ነበር። ሰው አትመስለኝ ብልህ ለልቤ ነው እንጂ ከልቤ አልነበረም። አትምጣብኝ ብልህ እንድትመጣ እንጂ ገፍቼህ አይደለም።

ብቻ. . . አሁን የመጣሁት ጥቂት መልዕክቶችን ሃሳቦች ይዤ ነው። ምን መሰለህ፣ አሁን ላይ ዛሬ ላይ ሰላምን እሻለው። ካልወደደከኝ ዘንዳ ፍቅርህን ከልክለው፣ ከእሷ ላይ ተላቀቅ ጥለህ ጥፋ በለው። ያው እንደምታውቀው  ብቸኝነት ላይ ነኝ፣ ሙቀቱ ሀሩሩ እኔ ላይ ይከፋል እና ያው ስትቀብረኝ ሳጥን አትግዛልኝ አፈር ይበቃኛል። ዋናው መልዕክቴ ግን አንድ እና አንድ ነው። ለአላፊ አግዳሚው ስሜን አታስነሳው፣ እሷ እኮ እንዲ ናት እሰይ የት አባቷ ይበላት አትበለኝ፣ አልፋለች ሞታለች አትበለኝ የኔ ዓለም፣ ሰውም ሳይሰማብን በሚስጥር ቅበረኝ።

Comments (0)
No comments yet