አ-ይድረስ ለ_

a-yederase-la

መድረስ አለመድረሱ ሳይሆን መገለጹ ዋጋው ትልቅ ነው።

" ደብዳቤ ልፅፍላት ፈልጌ ነበር። ውስጤ ያለውን በሙሉ ልነግራት፣የተሰማኝንን ላሰማት፣ያመመኝንን ላስጎበኛት እመኝ ነበር። ከዚህ በፊት ያልነገርኳትን በሙሉ ጨምሬ መፃፍ አምሮኝ ነበር። በህይወቴ ምን ያህል ዋጋ ሰጥቻት እንደነበር፣ራሴን ከማከብረው በላይ ምን ያህል እንዳከበርኳት ላሳውቃት እፈልግ ነበር። ያ ክብር እውነት ተገብቷት ይሆን? እሷስ ያ ክብር በእውነት ይገባኛል ብላ ታስብ ይሆን? አሁን ላይ እጠይቃለሁ። ጠላው ተንጠፍጥፎ ያለቀ ኩባያ ሲወድቅ የሚያወጣው 'ቋ' የሚል ባዶ ጩኸት ውስጤ ሲነግስ. . . ያኔ በጣም እጠላታለው። ከበደሏ በላይ እውነቴን ምን ያህል እንዳቆሸሸችው ሳስብ መሃል መንገድ ላይ ኩርምት ብለህ አልቅስ አልቅስ ይለኛል። ፍቅር የያዛቸው ሰዎች ልባቸውን እና ቀልባቸውን እንደሚሰራረቁ አውቃለው። ያው ባላውቅም ሲያወሩ እሰማለው፤ አምናቸዋለው። እኔ ግን እውነቴን ነው የተሰረኩት። ያልሆነ እና የሆነ አጋጣሚ ሀቄን በእሷ አስነጠቀኝ። ለሰው 'እንዲ ነው እኮ' ብዬ መናገር አቃተኝ። የእሷ ውሸት እና ዋይታ ቀድሞ ተሰምቶ ኖሮ የኔው የዘገየ እውነታ እና እንባ እንደ ተራ የፍቅር ዘፈን ተሰማ። ህይወቴን ሙሉ አግኝቶ ማጣት የሚያም ይመሰለኝ ነበር። ለካ እውነታን መነጠቅን የሚያህል ጉዳት የለም። እየጮሁ ግን ድምጽ ማውጣት ሲያቅት የሚፈጥረው ግራ የሚያጋባ አስጨናቂ ውጥረት። የኔ እና እሷ ህይወት በዚ ይገለጻል፤ ለእሷ የተመኘችው የሚሳካበት፣የሚሰምርበት ለእኔ የሚያንገበግብ ጠፍቶ የማይጠፋ ፊም የምሸከምበት።

ሰዎች እድላቸውን ሲያማርሩ እሰማለው፤ 'የአርባ ቀን እድሌ ነው ለዚ ያበቃኝ' 'ይህ ጠማማ እድሌ እንጂ እኔስ. . .' እድሌ ይሆን እንዴ ብዬ ጠይቄ አላውቅም። ከእሷ በፊትም በኋላም ከሰውነት የጎደለ አጋጥሞኝ አያውቅም። የሚያውቋት አንዳንዶች በእኔ ፊት ሰለሷ ሰውነት ሲያወሩ ሳቅ አይሉት እንባ ይገዳደረኛል፤ማውራት ግን ይከብደኛል። ያው አንደኛዬን ተራ የፍቅር ዘፋኝ ሆኜ የለም ማን ያደምጠኛል?። ክብሬ መልኬ የምል ሰው አልነበርኩም፤እከሌ ስለእኔ እንዴት ይህን ያስባል ብዬ ብዙ የምጨነቅም አልነበርኩም። በእሷ ምክንያት ያጣሁት ክብሬ፣ያጸየፈው መልኬ እና የተነሳው ስሜ ግን ከምንም ከማንም በላይ ይከነክነኛል። 'ፍቅር ይዞህ ነው እንዲህ የምትሆነው' ሲሉኝ ዝለል ዝለል ፍረጥ ፍረጥ ይለኛል። እውነት የሚያውቁት ፍቅር እንዲህ ከሁሉ የጎደለ ከብዙ ያነሰ ከሆነ አለማፍቀር በስንት ጣዕሙ።

ብቻ ከንዴቴ መስኮት ዘወር ብዬ እውነቴን ሀቄን ብጽፍላት፣ ልቤን ከሚጎትተኝ ቀለል ብሎ ከሚያስጨንቅ ስሜት ባጋራት፣ ከታፈነ በደሌ ባቋድሳት ደስ ይለኝ ነበር። ግና ቃል አነሰኝ። አለም ላይ ያለው ፊደል ሁሉ ቢሰደር ስሜቴን አንደማይገልጽልኝ ገባኝ። ለሰው ሁሉ የቀለለው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ለእኔ እንዳልሆነልኝ ተረዳሁ። ሆሄያትም እንደሸሹኝ አመንኩ። በአጭሩ ሁሉም አጠረኝ፤ ሁሉ ተንጠለጠለብኝ፤ ሁሉም።

ነገር ግን አማኝ ነኝና አምናለው። እውነቴ ነጻ ባትወጣ እንኳ፣ ለእሷ ግን አንዲትም ሳትዛነፍ ሳትጓደል የሚገባት እንደሚሰጣት፣ የሰራችው እንደሚጠብቃት አልጠራጠርም። ለኔም የቀን ባለጉልበት ይመጣና የዘራችውን ቀቅላ ስትበላ ያሰየኛል። ታዲያ አማኙ ልቤ ይህን ያውቃል፤ ያኔ እሷ ዕዳዋን ስታወራርድ እኔ ስለእሷ መኖርም መሞትም ግድ አይሰጠኝም፤ ያኔ እሷን አላውቃትም።"

Comments (0)
No comments yet