ንሴብሆ

neseebeho

ይኸውልሽማ በዚህ አለም ህግ መዋደድ ብቻውን ፣ የህይወት መስመር አይሰራም። ከኛ በላይ መዋደድ ባይኖርም ፣ It isn't meant to thrive ... ምናልባት ገነት የሚባል ነገር የእውነት ከሆነ እንገናኛለን ...

 የደብሩ አለቆችና ነጫጭ ፀጉር የሞላቸው ሊቀ–ካህነት ፣ በወርቅ እንዲሁም በብር መጎናፀፊያና ላንቃ  በተለበጠ ግርማው እጅግ በሚያስፈራው የቃልኪዳን ታቦት ኋላ ይታያሉ። አርምሞና ፅሞና ከደረቡት ረዥም አልባሰ ተክህኖ ጋር ፣ የኦሪት ነብይ ያስመስላቸዋል።ከታቦተ ህጉ ፊት ፣ ሀጫ በረዶ የመሰለ የቄስ ጥምጣም ያደረጉ በእድሜ በጥቂቱ የጎለመሱ ፣ ደርበብ ያሉ ቀሳውስት በፅናና  መቋሚያቸው ፣ ካባቸውን ደርበው በግእዝ ወረደ ወልድ እያሉ በለሆሳስ ወረብ ያወርዳሉ።  ከነርሱ ፊት እንደነብር ጣት የሾሉ ብርቅርቅ የዲያቆን አልባስ የለበሱ  ወጣቶች ፣ በከበሮ ታጅበው አውሎ ነፋስ የሚያስነሳ የቸብቸቦ መዝሙር ተያይዘዋል።

ግምግምታው ልብ ያርዳል ። ቃጭልና ማእጠንቱ አምሳለ ገነትን በእዝነ ህሊና ይከትባል።ነጭ ከለበሰው ምእመን ጋር እየተጋፋው ፣ በሩቅ የሚነደው ቅዱስ እጣን ሽታ ሽው ቢልብኝ ፣ከገላሽ የማይጠፋው    የChanel ሽቶሽ ትዝታ ከሆዴ ምንግል ብሎ ሲወጣ ታወቀኝ።

ተስፋ ... አንገቴን አቃናሁ ..."የመዳን ቀኔ ዛሬ ናት?" ...መጠየቄ አልቀረም።ልማድ ሆኖብኝ አጅቤ የመጣሁት ታቦት ... ከመንበሩ ሲደርስ ከሳምሶን ባላነሰ ጉልበት ተጋፍቼ ፣ ከባህረ ጥምቀቱ የፊተኛ ረድፍ ተሰለፍኩ። የሚረጨው ፀበል ሰውነቴን ድንገት አራሰው። ሳላስበው እንባዬ ዝርግፍ አለ። አልተከላከልኩትም። ሰውም አላወቀም።   "ተመስገን ..."  ሳይታሰበኝ የግልግል ፣ ከምጥ የመላቀቅ አይነት ደስታ ወረረኝ።(ፍቅርሽ እንባዬ ውስጥ ነው የተሰገሰገው እንዴ?) ያው ሀሳብ የገባኝ የ Charles Bukowski...The free soul is rare, but you know it when you see it—basically because you feel good, very good, when you are near or with them... ትዝ ቢለኝ ነው..  እተካሽ ይሆን?ይኸውልሽማ በዚህ አለም ህግ መዋደድ ብቻውን ፣ የህይወት መስመር አይሰራም። ከኛ በላይ መዋደድ ባይኖርም ፣ It isn't meant to thrive ...  ምናልባት ገነት የሚባል ነገር የእውነት ከሆነ እንገናኛለን።   ውሸት ፣ ገንዘብ ፣ ፉክክር  ምናምን በሌለበት ቦታ ... ማንም ከኔ አይነጥቅሽም።

ለጊዜው አብሮ መሆን ቢያምረኝም ፣ እንደጉም የማይጨበጥ ህልም ሆኖ ቀርቷል። ወዶ መለያየት  ብርቅ አደለም ...  እህል ውሀ ነው።አይገርምም?   አሁን... አሁን ...ግን ተስፋ ቆረጥኩ መሰል ...ሰማይ  ቀለም አለው፣ አእዋፍ ይዘምራሉ ፣ ጨረቃ እንደ ድሮ ታምራለች ... አሁን?  ትኩስ ቡና ይፋጃል ፣ ረሀብ ትርጉም አለው ፣    ጥርሴም ለቀልድ ይፈጋል  ፣ እንኳን ሌት ቀን እተኛለሁ።  አሁን?  ... አልወድሽም ባልልም  የሚያምር ሳቅ ሌላ ሴትም ላይ አያለሁ።ነገን የሚያውቅ የለምና ፣ የራሰ ነጠላዬን ሰብስቤ ተነሳሁ። ከበሮው አሁንም ሞቅ እንዳለ ነው። እንጃ ፣ ልረሳሽ ነው መሰል ተመስገን።

"ንሴብሆ ፣ ንሴብሆ ..."

Comments (0)
No comments yet