ዘንድሮስ ወዮልኝ!

1 min read
zanederose-wayolenye

የስራ ማጣት ሁኔታ የሚስከትለውን የስነ-ልቦና ችግር፣ ከቤተሰብ ጋር የሚፈጥረውን ሁኔታ ያሳያል። ወደ ኋላም መለስ ብሎ የዩንቨርሲቱ ህይወቱን ለመዳሰስ ሞክሮ አሁን ካለበት የስራ ማጣት ሁኔታ አንፃር ዩንቨርሲቲ ገብቶ መማርን ይመርጣል።

ዘንድ

ተመርቀን ከወጣን ግማሽ መንፈቅ ይዘናል። በተለይ አሁን የስራ ማጣት ሁኔታ እየተሠማኝ መጥቷል። ቤታችን እንቁላል ያስቀመጥን ይመስል ዩንቨርሲቲውን በፍጥነት ለቀን ነው የወጣነው። አንድም የትምህርት ማስረጃዎቻችን ስላጠናቀቅንና የመኝታ ፍራሾቻችንን ስላስረከብን ሌላም ተጨማሪ ምንቆይበት በቂ ገንዘብ ስላልነበረን ነው። እኔ መፍጠኑን ባልወደውም የጓደኛዬ የመሄድ ውሣኔ እና በጊዜው ድሬዳዋ ከተፈጠረው ግርግር ጋር ተዳምሮ ሀሣቤን በዛው መንገድ ልቃኘው ወደድኩ። በጊዜው የተማርነው አንድ ወሠነ-ትምህርት(ሴሚስተር) ብዙ አስለፍተውናል። ፈተናው፣ የተግባር ስራው በዛ ላይ የመመረቂያ ፅሁፉ በተለይ በአጭር ጊዜ ስለሆነ የነበረን ጫና እንዳለው መካድ አይቻልም። እውነት ለመናገር ጥሩ የጥናት ልምድ ነበረን ማለት እችላለው። ይህም መጀመሪያ ሁላችንም በግላችን እናጠናና በኋላ ተገናኝተን ደሞ በጋራ እንወያያለን። እንዳችን የገባን ላልገባን እንተጋገዛለን፣ እናጠናለን፣ እናስጠናለን። ይህም በኋላ ለመጣው ውጤት አስተዋጽኦ ሣያደርግ አልቀረም።

ሀረማያ ቤተ-መፅሀፍቱ የተለየ ነው። ለማንበብም የተመቸ ነው። አንዳንዴም ከንባብም በተጨማሪ ሌላም እድል ይዞ ይመጣል። አንዴ project 'ሚባል ኮርስ እያነበብን አይነ-ግቡ የሆነች ልጅ አልፋን ሄደች። እውነት ለመናገር ልጅቷ በጣም ታምር ነበር። በጣም እያየኋት ስለነበር ይህንን ጓደኞቼ አስተውለውት ኖሮ ሣቁብኝ። ለአንዱ ጓደኛቼ "ቤኪ" አልኩት አቤት ልጅቷን ይዘህልኝ ና ስለው ሣቀ። ከውበት አድናቆት ተመልሼ ወደ ንባብ ልቤን እያዞርኩ እያለ ለምን አታናግራትም አሉኝ ጠበቅ አርገው ኸረ ተዉኝ እያልኩ ወደታች አሻግረን ስንመለከት ከሌላ ልጅ ጋር ቁጭ ብላ እያጠናች አየን። በቃ እድልህ አይደለም ብለውኝ ንባባችንን ቀጠልን። ነገሩ በዚህ ይለፍ እንጂ ስለሷ በቀጣይ የሠማሁት የሚመስለኝ አ.አ ልሄድ አንድ ቀን ሲቀረኝ ነበር። የዶርም ልጆች ስለአንድ ልጅ ሁኔታ እያወሩ ነበር።

"ይቺን ምታምረዋልን ልጅ ታውቃታለህ?" "ቀዩዋ፣ አጠር ያለች ካፌ እንደውም እናያታለን እኮ... Babe" ምንምን እያሉ ያወሩት ስለሷ ይመስለኛል። ከዛ ቀን ጀምሮ ቤት ከገባሁም በኋላ ሀሣቤ ስለሷ ነበር። እውነት ለመናገር በራሴም የተናደድኩበት ቀን ነበር። በዛ ቅፅበት እሷን ለማናገር የሆነ ነገር ማድረግ ነበረብኝ ይሆን እላለው ምክንያቱም ከዛ በኋላ ደግሜ አላየኋትም ከዛ በፊትም ያስተዋልኳት አይመስለኝም። መልኳ ብዙም ባይሆን ውልብ ይልብኛል። የደስደስ ያላት፣ መልከ-መልካም፣ ደመ-ግቡ ነገር ነበረች፤ አይቻት ሳልጠግብ የጠፋች።

ለኔ 2014ትን ለሦስት እከፍለዋለው

1ኛው. የመጀመሪያውን 4 ወር ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀጥሬ የሠራሁበት።

2ኛው. 4 ወር በላይ በተማሪነትና ትምህርት ላይ የቆየሁበትና ምናልባትም የመጪውን ባላውቅም የመጨረሻውን የዩንቨርሲቲ ህይወት ያየሁበት።

3ኛው. የቀረውን 4 ወር አካባቢ በስራ-ፈትነትም ፣ በስራ-ፍለጋም ውስጥ ሆኜ አመቱን የጨረስኩበት ሆኖ አልፏል።

መቼም አዲሱ አመት ሲመጣ ደሞ እንደማንኛውም ግለሠብ እቅድ ይኖራል። ግን እቅድ ለማውጣት አዲስ አመትን ሁሌ ተገን ማድረግ ያለብን አይመስለኝም። አንዳንዴማ ዕቅዶቻችንን አዲሱ አመት ላይ በልጓም አስረነው ራሱ እንዲሳካልን ያደረግነው ይመስለኛል። ዘመን በጎ ሊሆን ይችላል ላይሆንም ይችላል። ያንን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ነገር ግን እኔ የማምነው ነገር እኛ ነን ዘመኑን ሠላምም ችግርም የምናደርገው የሚመስለኝ።

አንድ ዘመን ሲመጣ አንድም ዕድልን ሌላም አደጋን ሊያመጣ ይችላል። ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ለምሣሌ:- ጎርፍ፣ ድርቅ እና አምበጣ በቅርብ ጊዜ ካስተዋልናቸው ክስተቶች ውስጥ ይመደባሉ። በሠው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳትን አልፎም ስነ-ልቦናዊ ጠባሳን አሳርፈው ያልፋሉ።

አንድ ክፍል ውስጥ ስንማር መቼም ብዙ አይነት ተማሪ ነው አይደል ያለው፤ ከተለያየ ማህበረሠብ የመጣ፤ በተለያየ ባህል ውስጥ የተቃኘ ነውና "ጉራማይሌ" ነው። በባህሪውም እንዲያው ነው። ጎበዝ ተማሪ ሊኖር ይችላል እንደዛው ደሞ መኮረጅ የሚፈልግ ይኖራል። ፈተና ላይ የሚረብሸኝ ሠው አልወድም። በባህሪዬ ፈተና ላይ ከማንም ጋር መልስ መስጠት፣ መነጋገር አልወድምም፤ እፈራለሁም። እንደዛም ሆኖ ብዙ ልጆች በዚህ ጉዳይ ፈትነውኛል። የፈተና ወረቀታቸውን ሠጥተውኝ መልሱን ሠርተህ መልስልኝ ከሚል ጀምሮ እስከ መልሱን ንገረኝና ወረቀቱን ከፍ አድርገው እስከሚል ድረስ ማለቴ ነው።

ዩንቨርሲቲ ውስጥ ደስ ካለኝ አንዱ ነገር ቢኖር ሲኮርጁ የነበሩትን የክፍል ጓደኞቻችንን ወደ ንባብ ተመልሠው ፈተና ሲዘጋጁ ማየት ነበር። አንድ እረፍት ነው ሌላም ደስ የሚል ስሜት ይሠማኛል። ከኛ ጋር አብረውን ያነባሉ፣ እናስጠናቸዋለን እናም ሽምደዳውን በቃላቸው ይይዛሉ። ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ከሠው መልስ መጠበቅ ትተዋል ማለት አይደለም ግን ቢያንስ ሌላ አማራጭ ይዘዋል። ያነበቡትንና የሚያውቁትን በራሳቸው መስራት የከበዳቸውን መሞከር እድል ካገኙም መኮረጅ ነው።

አንድ ጊዜ ሀረማያ እያለው ፈተና እየተፈተንን እያለ አንዱ ጓደኛችን ጮክ ብሎ ጠራኝ። "ዞላ... ዞላ" አለ። ፈታኟ የኛ ዲፓርትመንት head ነበረች። ከአንዳንድ አየችው ድምፁም ተሠምቷታል። ና ውጣ አለችው። አስታውሣለው በጣም ነበር የተቆጣችው። እኔም ሁኔታው አላማረኝም ነበር። ብዙም አልቆየሁም እኔም ፈተናዬን ጨርሼ ወረቀቱን አስረከብኩና ከክፍሉ ልወጣ ስል ቀድማኝ በሩጋ ቆማ እዛው ቁም አለችኝ። እኔም ሁኔታው ስከገባኝ ቆምኩ። ያባረረችውን ልጅ ና አለችው በሩጋ ቆማ። ይዛው እንደገና ክፍሉ ውስጥ ገብታ ፈተናችንን አወጣችውና "ሁለታችሁ ናችሁ አደል ስትኮራረጁ የነበራችሁት" አለች ቆጣ ብላ። ኽረ እኛ ምንም አልሠራንም አልናት። በኋላም የሁለታችንን ፈተና ዜሮ ልትሠጠን የመሠለው ልጅ "አባቴ ይሙት እሱ ምንም አላደረገም እኔ ነኝ የጠራሁት ግን ምንም የሠራነው ነገር የለም ፤ እንደውም ፈተናችንን አስተያይው" አላት። አየችው እንደውም ፈተናው ከነበረው 20 ጥያቄ ምርጫ ባዶ ነበር የሠጠው ሌላም ያልሠራው ጥያቄ ነበር። እሱ ከመጥራት ውጭ ምንም አላረገም ነበር። ምንም እንዳልተፈጠረ ሲገባት እኔን አስጠንቅቃኝ እሱን ያልጨረሠውን ፈተና እንዲጨርስ አድርጋው በዛው አለፈ። የሚገርመው ልጁ ዶርም ድረስ መጥቶ ይቅርታ ጠይቆኝ እኔም "ምንም ችግር የለውም" አልኩት። እውነት ለመናገር ንፅህናዬን ስለማውቀው በጊዜው ያን ያህል የተሠማኝ ነገር አልነበረም። ትንሽ ለማዋከብ ሞክራ ነበር ግን በበጎ አለፈ። ከዛ ወዲህ ልጁን ፈተና ላይ በአይነ-ቁራኛ ነበር የምትከታተለው።

ዋናውን ሃሣቤን ከማንሣቴ በፊት "ሠበዝ" ከሚለው መፅሀፍ ውስጥ ተስፋ አስቆራጩ መምህሬ የሚለውን ፅሁፍ መነሻ ይሆነኝ ዘንድ እወዳለው። ታሪኩ ምንድን ነው...ደራሲው በጊዜው ጎበዝ ተማሪ እንደነበረና በጊዜው በዩንቨርሲቲው የመምህርነት ዕድል ሊኖረው እንደሚችልና ቢያንስ ቢያንስ ባህር-ማዶ ሄዶ የማስተርስ ዲግሪውን የመማር እድል እንደሚኖረው ያምን ነበር። ነገር ግን የታሠበው ሣይሆን ያልታሰበው ሆነና ከተመረቀ በኋላ የመንግስት ለውጥ የነበረበት ጊዜ ስለነበር ስራ በማጣት አንድ አመት አካባቢ ተቀመጠ። ስራ ካገኘም በኋላ ለስራ ሀዋሳ ሲሄድ በዛው ወንዶገነት ዩንቨርሲቲ ጎራ ብሎ ጓደኞቹን ሊጠይቅ ይገባል። ጓደኞቹ ጋርም ተገናኝቶ ብዙ ይጨዋወታል። በተለይ ብዙዎቹ መምህርነት ዩንቨርሲቲ ውስጥ ገብተዋል ሌሎቹ ማስተርሳቸውን እየተማሩ ነው። ይህንን መስማቱ ደራሲው እንደሚለው "ቅናት ቢጤ ይዞኝ ነበር" ብሏል።

"በዛው እንዳለ የቀድሞ መምህሩን አገኘና ሞቅ ያለ ሠላምታ ከሠጠው በኋላ መቼም አንተ ማስተርስ እየተማርክ መሆን አለብህ" አለው መምህሩ

የቀድሞ ተማሪው: "ኸረ አልጀመርኩም" አለው

መምህሩ: "አይ ግድ የለም ለነገሩ ልጅ ነህ ትማራለህ ግን አንድ ነገር ልምከርህ" አለው መምህሩ ምን አለ ጥሩ ጥቆማ የሚሠጠው መስሎት

መምህሩ: "መማር ከፈለክ እንዳታገባ" አለው

የቀድሞ ተማሪው: በጊዜው አግብቶ ስለነበር "ኸረ መምህር አግብቻለው" አለው ለመምህሩ

መምህሩ: "አይ ጥሩ ነው ግን ልጅ እንዳትወልድ" ይለዋል

የቀድሞ ተማሪው: በጊዜው ልጅ ወልዶም ስለነበር "ኽረ መምህር ልጅም ወልጃለው"

መምህሩ: "It.s ok ባለቤትህ ልጁን ትይዛለች 2ኛ ግን እንዳትወልድ" ይለዋል

በጊዜው ደራሲው 2ኛ ልጅ ከወለደ ወራት ተቆጥረው ነበር ለመምህሩ ለመንገር ቢከብደውም "2ኛም ወልጃለው" አለው

መምህሩም ተበሳጨና "ምንድነው ሚያስቸኩልህ አይ አንተ በቃ ተስፋ የለህም" ብሎት መምህሩ ጥሎት ሄደ።

ይህን ከተነጋገሩ 6 ወር በኋላ ደራሲው የት/ት እድል አግኝቶ በባህር ማዶ ተምሯል ብዙም ሣይቆይ PHDውን ተመርቋል። ፅሁፉን ሲዘጋ ያነሣው ሃሣብ ምንድን ነው ለሱ ባለቤቱ ልጆቹና ቤቱ ከሁሉ ነገር እንደሚበልጡና ሠው ከሚያስበው ይልቅ የፈጣሪ እቅድ እንደሚበልጥ ያወሣል። ለዚህም ማሣያ ሚሆነው ደራሲው ከተመረቀ 6 ዓመት ሆኖት እንኳን ማስተማረም ነበር። ዛሬ ግን ትልቅ ዶክተር ነው። ይህን ታሪክ ሳይ ራሴን እንድመለከት ነበር ያደረገኝ።

አንድ ቀን ማታ ላይ ጠሩኝ ወደ ሳሎን ስዘልቅ ልናናግርህ እንፈልጋለን አሉኝ። እኔም ፈራ ተባ እያልኩኝ ገባሁ። መቀመጫውን እየጠቆሙኝ እንድቀመጥ አሣዩኝ። ከፊታቸው መታዘብ እንደቻልኩት ጥሩ ነገር እንዳልሆነ ስለመሠለኝ ከመቀመጤ በፊት ጥሩ ዜና ነው ወይስ መጥፎ አልኳቸው ፈጠን ብዬ። ተቀመጥ አሉኝ ቁጣ ብለው ስሜት። ተቀመጥኩ። እስከመቼ ነው በስራ ማጣት የምትቀመጠው አሉኝ። እስኪ የጎረቤታችንን ልጅ እያት ባለፈው ቴክኒክና ሙያ ተመርቃ ቀበሌ ገባች። የሻሼ ልጅ እንግዲህ ነሃሴ 29 ነው የተመረቀችው ታስታውሣለህ ይኸው ወር ሣይሞላ ገባች እያሉ ስራ የገቡትን ምስክርነታቸውን ገለፁ።

የስራ ማጣቱን ጉዳይ ቀጥታ ያገናኙት ከተማርኩት department ጋር ነበር። father ለሚያውቃቸው ሠዎች ደውሎ ስራ እንዲያገኙልኝ ጠይቆ ነበርና ስለተማርኩት department ምን እንደሆነ ሲያውቁ ውይ አይ እኛ እንኳን ይሄን አይደለም 'ምንሠራው ብለው ይመልሳሉ። ምናልባትም በዚሁ መንገድ ብዙ ወዳጆቹንም ሆነ የሚያውቃቸውን ሠዎች ጠይቆ ምንም መፍትሔ ስላጣ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ አሣስቦት ነበርና መጨረሻ ላይ የጠየቀውን ሠውዬ ስለተማርኩት department father ነግሮት ውይ በዚህማ በቀላሉ አይገኝም ይሄማ terror ነው እንዳለው ከራሱ አንደበት ሠምቻለው። ይህም ክፉኛ እንዳናደደውና ተስፋ የማጣት ስሜትን ተገንዝቤያለው።

ይህን የማይረባ ትምህርት ተምረህ ምንም ካልጠቀመህ ምን ይሠራል ቢዝነስ ብትማር ኖሮ ሲል mother ከአፉ ላይ ቀምታ "ይኸው ጎረቤታችን ሃይሉ አማራ ባንክ የስራ ማስታወቂያ ያወጣል እዛ ለምን አይገባም ይለኛል።" አለችው። እሱም "አይይ መች አወቀ የተማረውን" ብሎ መለሠላት። ስንት ልጆች የተመደቡበትን የትምህርት ክፍል ሲቀይር እሱ ፈዞ ነው እንጂ አለ። እስኪ ጆኒን እይው Hotel management ደርሶት እያለ እንዴ ወደ ቢዝነስ የቀየረው ለነገሩ Hotel ቢማርም ሃይሌም ብዙ ሆቴል ሠርቷል አንዱ ጋር ይገባል አላት። ማነው የደረጄ ልጅ መንግስት ሌላ መድቧት አይደል እንዴ አሁን ተፈትና ዶክተርነት እየተማረች ያለችው ብሎ ዘረዘረ። ይሄን የትምህርት ክፍል የገባው እኮ ሒሳብ ላለመስራት ነው ብሎ የበፊት የትምህርት ታሪኬን የኋሊት በምናቡ ማስታወስ ጀመረ። እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ሒሳብ ጎበዝ ነበር አለ። እናቴም ቀባል አድርጋ ምነው ተሸላሚስ አልነበረ አለች። ከዛ ስንቴ ተመላለስኩ ት/ቤት በጊዜው ሒሳብ ጉዳይ አለ። ያ ሁሉ ልፋቴ ገንዘቤን ከስክሼ አስተምሬ ሲያልፍም በረሃ አብሬ ተንከራትቼ መጨረሻው ይሄ ነው አለ በንዴት። በዛውም አንድ ምሣሌ አከለበት።

አንድ ሸንኮራ ከምተክልና አንድ ጎመን ከምተክል የቱ ቀድሞ ይደርሣል አለኝ። ጎመኑን ከተከልነው በኋላ እንኳን 2ኛ ጊዜ ልንበላው ነው። ሸንኮራው ከተተከለ ቆየ እስካሁን ፍሬ የለውም። ጎመን ባጭር ጊዜ ይደርሣል። ሸንኮራው ግን ገና ብዙ ጊዜ ይቆያል አለኝ። አየህ የተማርከው እንደሸንኮራ ሆኖ እንካሁን አልተጠቀምክበትም። ጎመን ብትተክል ሲል ቢዝነስ ብትማር ማለቱ ነበርና ይሄኔ ባንክ ወይም ሌላ ድርጅት ተቀጣሪ ትሆን ነበር ማለቱ ነበር።

የነብስ አባታችን ጓደኛ የነበሩት ቄስ አንዳንዴ መጥተው ይጠይቁን ነበርና አንድ ቀን መጥተው መጨዋወት ያዝን። በንግግራቸው መሃል የኔ የወንድሜ ልጅ እኮ ንብ ባንክ ቀጠሩት፤ እንደውም ካንተ ጋር መቀሌ የነበረው እኮ ነው አሉኝ። ይህንን እናቴም ሠምታው ኖሮ ገርሟት ብዙ ተጨዋወቱ። ይህ ነገርም በእናቴ ልቦና ውስጥ የቀረ ይመስለኛል። እንግዲህ አንድ ዩንቨርሲቲ የነበረ እኩል ተመርቀው እንዴት ሣትል አትቀርም።

"አሁን ያለፈው አልፏል ወደኋላ የለም ስለዚህ መማር ይኖርበታል ወይ 2ኛ ዲግሪውን ውይ ደግሞ የኮምፒዩተር ስልጠና የ3 ወር ወይም የ6 ወርም ከሆነ ገብቶ ይማር" አለ father ጠንከር ብሎ። ሁለቱ እየተቀባበሉ ነገሩን ከተነጋገሩበት በኋላ እናቴ " እና ምን ትላለህ" አለችኝ አስተያየቴን እየጠበቀች።

ምንም አላልኩም ዝም.....በላ ተናገር....አሁንም ፀጥ

"ተይው በቃ ምን ያልፈለገውን በግድ ምን ልታደርጊው ነው" አለ father

ጥያቄው ሲበዛብኝ "እንዳስደሰታችሁ አድርጉ" አልኩ።

የውሣኔ ሀሣብ ለመቀበል እናቴ ብትጠብቀኝም ዝም ነበር ያልኩት። በዚሁ ነገሩ እየለዘበ ሄዶ የዋናውን በር እንድቄልፍ እናቴ ጠይቃኝ እሱን ከቆለፍኩ በኋላ ክፍሌ ድረስ ተከትላኝ መጥታ ምን እንደሆንኩ ደግማ ብትጠይቀኝም አጥጋቢ መልስ አልሰጠኋትም ግን እኔ ንቀት ለማሳየት ሳይሆን ምንም የምናገረው ስለሌለ ነው። ይህ የቤተሰብ ውይይት ሲጀመር በቁጣና በንዴት ስለነበር መደናገጥ ይኖራል። ከኔ ስንፍና እንዳለ አልጠራጠርም ግን ደግሞ ነገሮች እየታከቱኝ የመጡ ይመስላል። የአዲስ አመት መምጣት አስቀድሞና ከመጣም በኋላ ጅማሬው ላይ ሆኜ ይህ አመት ሊከብድ እንደሚችል አስቀድሞ የገባኝ ይመስላል። እንደቀድሞ የነበረኝ የትምህርት ህይወት አሁን ሊኖር እንደማይችል የታወቀ ነውና አዲስ ጅማሮ ሲመጣ ትንሽ መንገጫገጭም እንደሚኖር ይገባኛል። ከተማሪነት ወደ ሠራተኝነት ቀላል ሽግግር አይመስለኝም። ምናለ ፍኖተ-ካርታው እኛ ላይ በጀመረ ብያለው ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት ስል።

ቸር ሰንብቱ...ስራ ላጣ ስራ የሚገኝበት ዓመት ይሁን!

የስራ ፈትነት ዘመኔ የከተብኩት።

Comments (1)
No comments yet