ነፍሴ ይሻት

1 min read
nafesee-yeshaate

ከተመረቅኩ በኋላ በነበረኝ በቂ የስራ-አጥነት ዘመን የከተብኩት ሲሆን ከቀለም ትምህርት ባሻገር የእጅ ሙያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውጠነጠንኩበት ፅሁፍ ነው። ካለፈው የትምህርት ዘመን ከአሁኑ ጋር ያለውን ልዩነት እያወዳደርኩ ሃሳብ ለመሰንዘርም ሞክሪያለው።

መጣጥፍ

ነፍሴ ይሻት....

ክረምቱ ከገባ ወዲህ የእጅ ሙያ የመማር ፍላጎቴ እያየለ መጥቷል። ምናልባትም በአሁኑ ሰዓት የሶስዮሎጂ ምሩቅ መሆኔን ባውቅም ብቁ እንዳልሆንኩ ይሠማኛል። የእጅ ስራ ክህሎትን እንደ አንድ አጀንዳ ይዤ ከቤተሠቦቼ ጋር ነጋ ጠባ ስለእሱ እያወራው አሠልችቻቸዋለው። በውስጤ ከሚመላለሱ ነገሮች መካከል የኤሌክትሪክ ሙያን እንደው ቴክኒክና ሙያ ገብቼ የአጭርም ጊዜ ስልጠናም በወሰድኩ እላለው። ምናልባት ሜክሲኮ የሚገኘው ተግባረ-ዕድ ት/ቤት ለኔ ጥያቄ መልስ መስጠት ይችላል።

ከዛ በተጨማሪ የስፌት ሙያና ጥልፍ በኪሮሽ መስራትን ከጊዜ ወዲህ እየተሣብኩ መጥቻለው። ማወቅን የመሠለ የለም እውነት ለመናገር ስራ ፆታን ሣይሆን መግለፅ ያለበት ክህሎት እንደሆነ ነው። ነርስን እንደሴት ዶክተርን ደግሞ እንደወንድ እንቆጥራለን ፤ secretary ለሴት manager ለወንድ ብለን እየከፈልን(gender division of labour) ልክ ያልሆነ ግንዛቤን ያዳበርን ይመስለኛል።

የምግብ ሙያን የማወቅ ፍላጎቴም ቢሆን ከኤሌክትሪክ እና ከስፌት ሙያ ባልተናነሰ መልኩ እየተሣብኩ ነው። የምግብ ሙያን እና ማጀትን ለሴት የተተወ ይመስለኝ ነበር ማለት እኔም የማህበረስቡ አካል ነኝና አስተሳሰቤና አመለካከቴ የዚህ የማህበረሠብ ቅኝት ነው። ነገር ግን ባለፈው የማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ የተመለከትኩት ነገር ቀልቤን ስቦኛል። "Cooking is not a gender role rather skill." የሚል። በተማርኩበት የትምህርት ክፍል ከሚሰጡ ኮርሶች መካከል Gender and society ነበርና በእርግጥም ይህ ት/ት አመለካከቴን የቀየረው ይመስለኛል። ሠዎች ሲፈጠሩ ፆታቸው ወንድ/ሴት ይሆናሉ። በፆታቸው ምክንያት የሚሰጣቸው ትርጉም የተለያየ ነው። ትርጉሙ በማነው ሚሰጠው ስንል በማህበረሰቡ።

በርግጥ ማህበረሰባዊ የአስተሣሠብ fallacy ወይም "ህፀፅ" በአንድ ጀንበር መፍታት ሣይሆን ቀስ በቀስ የሚስተካከል ይሆናል። ምግብ ማብሰል ለሴት ልጅ የተተወ ስራ ነው ስንል በእኩልነት ሠበብ ደሞ ስራውን ወይም ሙያውን እንድትተወው አይደለም። ባህር ማዶዎቹ equality ብለው በሠበኩን ንግርት ሴቶች ማጀት መግባቱን እየሠነፉ ይመስላል። ያ ግን ልክ አይደለም ሁለቱም በስራው ላይ ተሣታፊ እንዲሆኑና ሁለቱም እኩል ተጠቃሚነትን እንዲያረጋግጡ እንጂ።

የፀጉር ስራ ሙያም የመማር ፍላጎቴም ቢሆን ቀደም ብዬ ከጠቀስኳቸው ጋር የሚደመር ነው። ከሹሩባ፣ ቁጥርጥር እና ሳዱላ ጀምሮ እስከ ካስክ እና ተኩስ መቻል ፍላጎቴ ነው። በተለይ ደሞ ሹሩባና ቁጥርጥር ይበልጥ ብችልና እንደው እንደ እ/ር ፈቃድ የትዳር አጋር ብትኖረኝና ጊዜ ባለኝ ሠዓት 'ቆንጆ' አድርጌ ብሠራት እላለው አንዳንዴ በሃሣብ ውስጥ ሆኜ።

ወደኃላ ተመልሼ የት/ት ፖሊሲያችን ምን ይመስላል ብዬ ማሠብ ጀመርኩ። ሁሉን ከራስ መጀመር የተሻለ ነውና ግሎሪ ት/ቤት ስንማር እንዴት ነበር ብንል ትምህርታችን theory(ፅንሠ-ሃሳብ) ላይ የተመሠረተ እንጂ ተግባር ተኮር መሆኑን እጠራጠራለው። ምናልባት የተማሩ ጓደኞቼ ይህንን ሊያግዙኝ ይችላሉ።

[1] በchemistry የት/ት ዘርፍ ብዙ የቤተ-ሙከራ ጊዜያትን ማሣለፍ እንዳለብን ይሠማኛል። የሄድነው ጥቂት ጊዜያትን ነው። ምናልባት የሚያነሱት ችግር አንዱ የጥሬ እቃ እጥረት ነው ይህም በጀት በአግባቡ አለመመደብ ይመስለኛል።ቤተ-ሙከራ የሠራነውን Report እንድናቀርብ ቢደረግ ተማሪው ተማሪው ያገኘውን የተግባር ት/ት ምን አንደሚመስል አርቅቆ፤ በሚመች መንገድ አቀናብሮ የመፃፍ ችሎታውም ይጨምራል ባኝ ነኝ። 9ነኛ ክፍል እያለን "Science fair" ተብሎ አንድ ሣምንት ሙሉ ት/ት ተቋርጦ ነገር ግን እየመጣን ሣይንሣዊ ፈጠራ እንድንሠራ ና ስዕል እንድንስል መመቻቸቱን አስታውሳለው። በሣምንቱ መባቻ ላይም አቅርበን ወላጅ መደሠቱንም አስታውስላለው።

እንደውም በሠው የፈጠራ ስራ እኛ መሞገሳችን አይረሣኝም። ነገሩ እንዴት ሆነ ንጉስና ዮሐንስ ይዘውት የቀረቡት የፈጠራ ስራ ነበርና ይህንኑ እያቀረቡ ሳለ በመሃል አንድ ክፍል ከሚበልጡዋቸው ከሱራፌልና ከአማር ጋር ለመደባደብ ብለው እኛን አቅርቡልን ብለው ወደ ጦር ግንባር ይሄዳሉ። እኛም እሺ ብለን እያቀረብን የአዶንያ አባት የኛን ስራ ካሳየናቸው በኃላ ወደነ ንጉስ የፈጠራ ስራ ገባን መሬት ስር የተቀበረ alarm ነበር ሌባው መሬቱን ሲረግጠው ይጮሃል አልናቸው። በኤሌክትሪክ የሚሰራ ስለሆነ የቤቱ ባለቤቶች ሊተኙ ሲሉ ያበሩታል። ስለዚህ አገኘው ብሎ ሲገባ sensor ስላለው ይጮሃል የሚል ነበርና እየነካን አሣየናቸው ። ተገረሙ ጥያቄም ጠየቁን መጨረሻም " i appreciate ብለው የደንብ የማላስታውሰው እንግሊዘኛና አማርኛ ቃላትን ከተናገሩ በኃላ አዶንያን ግንባሩን ሣሙት እኔም ቁልጭ ቁልጭ አልኩ። ያብራራሁት እኔ የትሣመው ሌላ ሆኖ እርፍ!

የኛ ትውልድ አንዳንዴ ትንሽ በሙያ ጉዳይ የተጎዳ ይመስለኛል። ምናልባት አንዳንድ ሠው በራስ ተነሳሽነት ራሱን ለማብቃት ከሚያደርገው በዘለለ ተደራሽነቱ ያጠራጥራል ምክንያቱም የሙያ ት/ት የሚሠጠው 10 ወይም 12 ውጤት ላልመጣለት ነው። ስለዚህ የሙያ ት/ት የተሠጠው ግምት አነስተኛ ነው። የቤተሠቦቼን ሠርተፍኬት ስመለከት የእርሻ ትምህርት ፣ ኑሮ በዘዴ(Home economics) እና የእጅ ስራ ተብሎ እንደ chemistry , biology እና physics ሲሠጥና ውጤት ሲያዝበት አይቻለው። በሌላ በኩል ደግሞ የተረውን ትውልድስ እንዴት እየተጠቀምንበት ነው የሚለው በራሱ ጥያቄ ያስነሣል። በደርግ ዘመን ዘመቻ ነበር ወጣቶች ተሠብስበው ተወስደው የገበሬውን እርሻ ጉልጓሎ ፣አረም ማረም ፣ አጨዳና ውቂያ ያግዙ ነበር። በዘመቻ ያልተማረውን ማህበረሠብ ክፍል ገጠር እየገቡ መሠረታዊ ትምህርት ያስተምሩ ነበር። ለምሣሌ፦ መሠረታዊ የሂሣብ ስሌቶችን(+ - × ÷) ማንበብና መፃፍን እና ገንዘብ መቁጠር እና የመሣሠሉትን ከዛም ባለፈ ደርግ ወጣቱን እየጠለፈ ወደ አውደ-ግንባር እንደሚያሠልፋቸውም ታሪክ ያስረዳናል።

ከትምህርታዊ ክህሎት ባሻገር አንዳንድ ተግባራዊ ክህሎትን የማወቅ ፍላጎቴ እየጨመረ መጥቷል። ለምሣሌ፦ ፈረስ ጉግስ ወይም ግልቢያ እና ውሃ ዋና ማንሣት ይቻላል። ወደ ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት የነገስታት ልጆች በልጅነታቸው ፈረስ ግልቢያ ፣ ዋናን አደንና ጦረኛነት ይማራሉ። መፅሀፍትን ደግሞ ሊቃውንት ተመድቦላቸው ቤተ-መንግስት አልያም እስኪነግሱ ድረስ በጥብቅ ጥበቃ አምባ-ግሸን ውስጥ ተጠብቀው ይኖራሉ። በጊዜው የአገው ምድር እና መተከል ለአደን ተመራጭ እንደሆኑ የሚታወቀው በብዛት ነገሥታት ለአደን እንደሄዱ በታሪክ የሚጠቀስ ቦታ ስለሆነ ነው።

እነዚህን ማወቅ ለኔ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለው። MA እና Phd መያዝ ብቻውን በቂ አይደለም በትምህርታዊ እና በተግባራዊ ክህሎት መደገፍ ካልተቻለ እላለው። እነዚህን ለመማር እድሜዬ አልፎ ይሄን? ወይስ ጊዜዬ ገና ይሆን? 6ኛ ወይም 7ተኛ ክፍል የምሆን ይመስለኛል ህፃናት ግቢ ገባንና ልጆች ዥዋዥዌ፣ እሽክርክሮሽና ሌላም እየተጫወቱ አየሁና ለአዶንያ ይመስለኛል እኛማ በቃኮ አረጀን ይሄ ጨዋታማ አልፎብናል አልኩት እንደድንገት በአጠገባችን ምታልፍ የት/ቤቱ ሠራተኛ የነበረች በኃላም እኔ 10-12 ክፍል በነበርኩበት ጊዜ የቤተ-መፅሀፍት ሠራተኛ ነበረች ስታልፍ ሰማችንና ሁለተኛ እንዲህ እንዳትል ብላ ተቆጥታኝ ሄደች። ለነገሩ እውነቷን ነው ለመማር አሁንም ፍላጎት ካለን እድሜያችን ሊገድበን አይችልም።

ዩንቨንሲቲ ከገባው በኃላ ጓደኞቼ የነገሩኝ አንድ ታሪክ ነበር ልጂ ኳስ ተጨዋች መሆን ብቻ ነው 'ሚፈልገው እና ሁሌ ሜድ ነው ውሎው። የራሱ ኳስ ነበረው እና ትምህርቱን እየተወው መጣ። በኃላም ጓደኞቹ አሳሳቢ እየሆነ ሲመጣ ቢነግሩትም እሱ ግን እኔ ኳስ ተጫዋች መሆን ነው 'ምፈልገው ይል ነበር። ምናልባት ከአንድ ሴሚስተር 'ሚበልጥ አይመስለኝም ዩንቨርሲቲ የቆየው። ይሄንኑ የመሆን ፍላጎቱን ይዞ ይመስለኛል የተጫረው።

ምናልባትም የ19ዓመት እድሜ የሚሆነው ይህ ወጣት በዚህ እድሜው ፍላጎት ስላለው ብቃትም ቢኖረው ዘሎ ኳስ ተጨዋች ሊሆን ይችላልን?

ታዲያ ቅድም የፈለግነውን ለመሆን እንችላለን በፈለግነው እድሜ አላልንምን? ብለን ጥያቄን በጥያቄ መመለስ እራሱ ህፀፅ(fallacy) ሊያመጣብን ይችላል። በዚህ አንፃር ይህ ሃሳብ ለመጠቅለል ያህል መሆን የምንፈልገውን ነገር መሞከር እና በዛም መፈተን(challenge) ይገባናል። ነገር ግን ሁኔታዎችን ግን እንደሚወስኑን ማወቅ ይገባናል። ሁኔታዎችን መርምረን እነዚህን እነዚህ ነገሮች ያዘልቀናል ብለን ብናያቸው መልካም ነው። በ19 ዓመት ኳስ ተጨዋች መሆን ባይቻልም እድሉ እጅግ ጠባብ እንደሆነ ግን መረዳት ይቻላል።

መልካም ቀን

ዘላለም ልዐልሠገድ

ነሃሴ ፪፩፲፬

Comments (0)
No comments yet