4ኪሎን ሽቅብ ሳማትር

1 min read
4kilone-sheqebe-saamaatere-1

4 ኪሎ ሆይ! አንተን አብጠልጥዬ ባንተ ስም መስኮቤን አወደስኩ። አንተን ሳነሳ ስላንተ 'ምተርክ አይምሰልህ። አንተ ለኔ መገናኛዬ ነበርክ። በጊዜያት ውስጥ ቆመህ ሠውን 'ምታስተናግድ ጠጅ አሳላፊ፤ ተጓዥን 'ምታስተናብር አስተናጋጅ ነህና።

(ይድረስ : ደብዳቤዬ ለወዳጄ: ልቤ)

ሰላም ላንቺ ይሁን መስኮቤ እንደምንድን ነሽ ፈጣሪ ይመስገን እኔም እንዳለው አለው በአካለ ስጋ ከተለያየን ድፍን አመት አለፈ። የጊዜው ነገር ይገርማል ። በዚሁ የመራራቅ ጊዜ እንኳን ከአእምሮዬ ልትጠፊ አልቻልሽም ። በምናቤ ወደ ኃላ አንቺን ሳስታውስ በውስጤ ትመላለሻለሽ። እርሱ ከፈቀደ በቅርቡ ሳላይሽ አልቀርም።

በአመት መቆራረጥ ውስጥ የተዳፈነ ፍቅር...

የደረጃ ስልጠና ከተጠናቀቀ በኃላ ሁሉም ወደ ቀድሞ ኑሮው እንደሚመለስ ፤ የተሰበሰበውም ሰልጣኝ ተበትኖ በየፊናው ስራ ፍለጋ እንደሚሰማራ፤ ቀድሞ ስራ የነበረውም ያለውን አጥብቆ እንደሚይዝ ልብ ይሏል!

ከዛም ውስጥ እኔ አንዱ ነኝና ስራ ፍለጋ 8 ወራትን ከተንከራተትኩ በኃላ አሁን እየሰራሁበት ያለሁበት ስራ አገኘው። በዚህም የቤተሰቦቼና የጎረቤቶቼን የስራ ጀመርክ ጥያቄ አሰታገስኩኝ።

በደረጃ ስልጠና ለኔ 3 ነገሮች አገኝቻለሁ ማለት እችላለሁ።

1ኛ)ሰው እንድተዋወቅና experience share እንዳደርግ

2ኛ) የመ/ር አቤሴሎም ትምህርት እራሴን እንዳይ አድርጎኛል ።

3ኛ) 'ባንቺ ፍቅርም እንድወድቅ ሆኛለሁ (በአጭሩ ልብ ልገዛ ብሄድ ልቤን የተበላሁት እዛው ነው ያውም በአንዲት መስኮብ እንስት)። በሚገርም ሁኔታ አሁንም ላንቺ የፅሁፍ መልዕክት መላኬን አልተውኩም ትናንት እንኳን አንድ አባባል ጣል አድርጌ ነበር ቅሉ! ምን ያደርጋል ከቦለክሺኝ በኃላ የላኩልሽ መልዕክት እንደማይደርሱሽ በቅርቡ ነበር የገባኝ። ምናልባት የቴክኖሎጂ ባዳ ሆኜ ይሆናል። እኔ ላንቺ እልካለሁ የሚገባው ቴሌ ጋር ነው። ይሄኔ ለሱ ቢመስለው ኖሮ የአንድ ወር የኢንተርኔት ጥቅል በነፃ ጀባ አይለኝም ብለሽ ነው።

ሁሌም መልዕክቱ እንደገባ ነው ነገር ግን ወዳንቺ ስልክ አይገባም። ቢገባም ፍቅሬ የገባሽ አልመሰለኝም። መስኮቤ! አንቺን ማስጨነቅ አልፈልግም ። መልስሽ አይሆንም እንደነበር አልዘነጋሁም ግን ይሄ መልስ እኔ አንቺን ከማፍቀር ሊያግደኝ አይችልም። የሀሳብሽን ይሁንታ ታፀድቂልኝ ዘንድ አልያም ነገሩንም ቀልብሼ ወደ እኔ ማመጣሽ ከሆነ አላውቀውም ግን ለዚህ ሁሉ በአካል ተገናኝተን የልብ ልባችንን ተነጋግረን እንድንፈታው ልብሽን ትከፍቺው ዘንድ ወደድኩ።

* * *

በሀሳብ መርከብ እየተሳፈርኩ በፍቅር ማዕበል ስናወጥ ከሃሳብ ጥልቀት እንድወጣ መልሕቅ የጣሉልኝ የስራ ባልደረቦቼ ነበሩ። አንዳንዴ በውስጣችን ያፈነውን እሳቤ በቅርብ ላሉት ስንነግር እንዴት ይቀላል። በዛ ላይ የመፍትሄ ሀሳብን አፍልቀው ሃላፊነትን ደርበው የእኔ የፍቅር ታሪክ እንዲሳካ ራሳቸውን ተዋናይ ሆነው መገኘታቸው ይገርማል። ከሃሳብ በዘለለ ራስን ለተግባር የመስጠት ልግስና ብል ማጋነን አይሆንም ። ይህን እንድል ያደረገኝ ነገር ቢኖር አንዱ የስራ ባልደረባዬ ያደረገልኝን ውለታ በማስታወስ ነው።

ክንፍ ያለው አሞራ ከዛፍ ይሟገታል፣

ከሚወዱት ጋራ ማን ሲኖር አይቶታል።

ሁሉም ሰው ከወደደው ጋር ማን ሲኖር አይተናል። በፍቅር የታበደላቸው የተባሉቱ ሰብለ እና በዛብህ እንኳን ፍቅራቸውን ከግብ ሳያደርሱ መቃብር ወርደዋል።

ከጓደኞቼ ያገኘሁት ምክር አዘል ቢጤ ውስጥ አንድ ሴት ላይ ብቻ የሙጥኝ ማለት እንደማያስፈልግና የራስን አቅጣጫ መፈለግን ነው። በእርግጥም ከአንቺ ውጭ ስንት ቆንጆ እንስቶች በሞሉባት አዲስ አበባ አዱገነት ውስጥ አንቺ ላይ እንደ 4ኪሎ ሽቅብ ማማተሬ “ጉድ ነው የአንኮበር ቅጠል!” ቢያስብልም የትኛውም ቆንጆ፣ የመኳንንት፣ የቢትወድድ፣ የጭቃ ሹም ልጅም ዘመድም ቢሆኑም ግድም የለኝ። መስኮቤ ከወይዛዝርቱም፣ ከግንብ ጠባቂውም ከልዕልቱም ከእልፊኝ አስከልካዩም ትልካለች እንጂ አታንስም።

ይህችን ሀመልማላዊት መስኮብ ከጥንቱም ንጉስ ስናነግስ ከግሸን አምባ ውስጥ አውርድን ወደ ቤተ-መንግስት እንደምናስገባ እኔም በልቤ ውስጥ ባነገስኳት ቤተ-መንግስት ውስጥ በፍቅረ-ሲመት ገብታ በክብር ታጎናፅፈኝ ይሆን? እንጃ ልቤ ክፍት ነው። አሁንም የንግስቷን መምጣት ይጠባበቃል። የነጋሲ ዘሮች ለንግስና እንደሚጣሉት አይደለም። ራስ ቢትወደዶችም አመፃቸውን ሊያነሱበት የሚችሉት ቦታም አይደለም። ክፍቱን ሆኖ የሚጠብቅስሽ ርስት እንጂ።

* * *

ዛፍ በሞላበት አሞራ መብረር እየቻለ ዛፍን የሙጥኝ ማለቱ ግርምትን ቢጭር አይገርምም። አንድ ዛፍ ከሌላው እያማረጠ እንዳሻው ቢፈነጭ ማን ተው ይለዋል መብቱ ነው!

ግን ይህ አሞራ ከዛፍ ዛፍ እየመረጠ ሲወላውል በአንዱ መታገስ ሳይችል ሲንገላወድ

በአንዱ ቦታ ረግቶ ጎጆ ሳይቀልስ፣ ከመስቀሌ-ብርሃኔ እያል ቢላወስ፣

ለዛፎች እንግዳ ለአገሩም ባዳ የሆነስ።

የቸገረ ቀን ወዴት ይድረስ። ክንፍ ያለው አሞራ ከዛፍ ይሟገታል።

4ኪሎን ሽቅብ ሳማትር!

ጥቁር አዞ የመሰለው አስፓልት፤ እንደ መቀነት ወገቧን ሸብ አድርጎ የሚታየው መንገድ ዛሬ ላይ ፈርሷል። አደባባዩን ታከው የቆሙ የድሮ መስሪያ በቶች ወድመዋል። የፍቅረኞች መቀጣጠሪያና የተማሪዎች መገናኛ የነበረው ታሪካዊው ጆሊ ባር ፈርሷል።

አጠገቡ የነበረው ግዙፍ የደረጃ መወጣጫዎች 4ኪሎን ፊት ለፊት ወግኖ የያዙት የብረት ፈለቆች የለም። የስራ ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው ቦርዶችም ጠፍተዋል። አሁንም ወደ ስራ፣ ትምህርትና የግል ጉዳይ ለመሄድ ሰው ይራወጥባታል። መኪኖች በረጅም ሰልፍና ክላክስ ታጅበው ይጎርፍባታል። ዛሬም 4ኪሎ በጠለሸው ውበቷ፣ በፈረሰው አካላቷ ላይ ሆና የሚሄዱባትን ታስተናግዳለች። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን 4ኪሎን ሳማትር አንቺ ትታወሽኛለሽ፤ በትናንትና ውስጥ የእንደ ሃውልቱ የቆምሽ መታሰቢያ ሆነሽ።

Comments (0)
No comments yet