የደካማው ጸሎት

1 min read
yadakaamaawe-tsalote

ለአህያ ማር አይጥማትምና ለማሩ ጌታ ምኑ ነው?

"ሰላም ላንተ ይሁን የሰላሙ ባለቤት፣ የክብሩ ሁሉ ወሳጅ እኔ ልጅክ ይኸው እንደለመድኩት አንተን ልማጸን መጥቻለው። አምላኬ ሆይ ያኔ የሰው ነገር ሳይገባኝ የፍቅርን ትርጉም ሳላውቅ እንዲህ ብዬ ጸልዬ ነበር። 'መቼም ቢሆን የማልወዳቸውን፣ የማልፈቅዳቸውን ሰዎች ወደ ህይወቴ አታምጣቸው፣ እንዳላስከፋቸውም እንዳላስቀይማቸውም። የሰውን ስሜት መጉዳት አንተን ማስከፋት ነውና።' ይሄን ጸሎቴን አብዝቼ እጸልይ እንደነበር አንተም ታውቃለህ። እንደሰማኸኝም አውቃለው በህይወቴ አይቼዋለውና። የሰማዩ አምላክ፣ የፍቅሩ ባለቤት አንተ አታውቀው የለ ያኔ ይህን ስመኝ ልቤም ንጹህ ሀሳቤም ጥሩ ነበር። ሴቱን እንዳንተ መልካም ፍጡርነት አክብሬው ወንዱንም በሰው ልክ አስቤው የመጣውን አክብሬ እና ወድጄ አስተናግድ እንደነበር አንተም አይተሃል። የኋላ ኋላ ግን የሰው ማንነቱ የልቡ ክብደቱ የሃሳቡ ክፋቱን አየሁት። እኔ ስሮጥ እነሱ ሲራመዱ እኔ ሳለቅስ እነሱ ሲስቁ እኔ ስጨነቅ እነሱ ሲተኙ ብዙ ታዘብኳቸው። ሰው ሁሉ ቢመሳሰልብኝ ግራ ገባኝ። ጸሎቴ ነው እንዳልል ስሜታቸውን እንዳልጎዳቸው የማልፈልጋቸውን አታምጣብኝ አልኩ እንጂ የሚጎዱኝን ላክልኝ አላልኩም። ችግሩ ከእኔው ነው እንዳልል ከሰውኛ ስህተት በላይ ገፍቼ ሄጄ ያስቀየምኩበት፣ ባስቀይም እንኳን ይቅርታን ያልጠየኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። ብረሳው አንተ ታውቃለህ። ታዲያ ፈጣሪዬ በየቱ ክፋቴ በየትኛውስ ተንኮሌ ይሆን የሚያስከፋኝ፣ የሚንቀኝ ከፍም ብሎ ተጥቅሞ የሚጥለኝ ብቻ የሚፈራረቅብኝ? እናም አምላኬ ሆይ አሁን የሰው ውስጠ ምስጢሩ ገብቶኛልና ጸሎቴን እቀይር ዘንድ መጥቻለው። አሁን ላይ ሰውም ክብር ማይወድለት ምግባር የጠላበት ነውና ያን የየዋህ ምኞቴን የጅል ሃሳቤን መቀየሬ ግድ ሆነብኝ። እናም አምላኬ ሆይ የሰውነት ክብር፣ የማንነት ጥንካሬን እሻለው። የሚወዱኝ የማልወዳቸውን፣ የሚያከብሩኝን እኔ ከቁብ የማልቆጥራቸውን፣ የሚንከባከቡኝ እኔ ግን ጀርባዬን የምሰጣቸውን የተወሰኑ ሰዎችንም ላክልኝ። ምናልባትም የዛኔ ዓለም ለኔ ብቻ እንዳልከፋች ለሌላውም እንደጠመመች ይሰማኝ ይሆናል። ሰው ለሰው መስታወቱ ነውና ሌላው ያሳየኝን ዋጋ ቢስ መልኬን የሚያስረሱ ከሚገባኝ በላይ ክብሬን የሚክቡ ጥቂቶችን ለኔም ትሰጠኝ ዘንድ እሻለው። አምላኬ ሆይ የሚወዱኝ የምወዳቸውን፣ የሚያከብሩኝ የማከብራቸውን ብቻ ስጠኝ እንዳልልክ ዓለም በእኩልነት አትመራምና ላስጨንቅክ ለኔና ለመሰሎቼ ብለክም ስርዓተ ዛቢያዋን ቀይር ማለቱ ቢከብደኝ እንጂ ሳላስበው ቀርቼ አይደለም። እና የልቤን ሰሚ ጸሎቴን ፈጻሚ ፈጣሪዬ ሆይ ከሁሉም አይነት ሰው ላክልኝ። በአንዱ ስከፋ በአንዱ እንድጽናና ለአንዱ ስሰጠው ከሌላው እንድቀበል ከዚኛው ሲጎድል ከዛኛው እንድሞላ። አደራህን አምላኬ ጸሎቴን ቀይሬያለውና የቀድሞውን ጸሎቴን አትቁጠርብኝ። ይኼኛውን ስማኝና እኔም እንደ ሰዉ ባልተገባኝ ቦታ ተቀምጬ የሚገባኝንን ፍቅር ና ትህትና አውጥቼ ልሽጠው። ዓለም አህያ ሆናብኛለችና ማሬን ከድኜ ላስቀምጠው። በሰው ዝቅታ ውስጥ ራሴን ላንግሰው። ፈጣሪዬ ሆይ ከሰውነት አውርደህ እኔንም እንደሌላው እንዳብዛኛው ሁሉ ከሰው በላይ አርገኝ። አሜን!"

Comments (0)
No comments yet