ኡኡኡ... የፈረንጅ ቡዳ በላን

uuu-yafaraneje-budaa-balaane

ፈረንጅ ሲጨማለቅ ያረገውን አይተን ለእርሱ የጠቀመው መስሎን እኛም ተከትለን አሁን እነርሱም እኛም ማጣፊያው አጥሮናል። የፖርን ሱስ ኡኡኡ ይልቀቀን!!!

የሆነ ልጅ ነኝ። ይኸውላችሁ አሁን አዲስ የመጣውን Bing AI Chat ከፈትኩና ‘’How many porn viewers are there in Ethiopia?’’ ብዬ ጻፍኩለት። ለምን ይህን ጠየቅኩ? በኋላ እነግራችኋለሁ። Bing AI ፍጥን ብሎ '’Hmm…let’s try a different topic. Sorry about that. What else is on your mind?'' የሚል መልስ ሰጠኝ። Bing AI Chat እንግዲህ የዓለም መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በማጠናቀር ጥያቄ ሲጠየቅ የሚመልስ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው። ታድያ በዓለም አለ የተባለ መልስ ሰጪ ሲከዳኝ እልህ ቢይዘኝና ጠለቅ ወዳለ መርመራ ብገባ እኮነናለሁ? አልኮነንም። ደግሞ ከተኮነንኩም ልኮነን እንጂ ይሄንን ርዕስ እስከጥግ ሳንጋፈጠው ዳር ዳር ስንል እኮ እያጥለቀለቀ ገደል ሊጨምረን ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፈረንጅ ባመጣብን የፖርን ቡዳ ተበልተናል። 

Bing AI እምቢ ካለ የተከበሩ ጋሽ Google አሉልኝ፣ ወደሳቸው ዓይኔን አዞርኩ። ጋሽ Google ምንተፍረታቸውን ከሸጡት ከራርመዋል፤ ያኛውን ስጠይቀው ያፈረውን እኚህኛው አዥገረገሩልኝ። ‘’How many porn viewers are there in Ethiopia?’’ ብዬ ENTER ከመንካቴ ብቻ 17,000,000 results in 0.34 seconds ብሎ ዝርግፍ። ከሁሉም በላይ የመጣልኝ በPDF format ያለ አንድ The Influence of Exposure to Pornography among the Youth in Addis Ababa የሚል የጥናት ጽሑፍ ነው። ከፈትኩት።አማኑኤል ተፈሪ የሚባል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት የማስተርስ ተማሪ የሰራው Thesis ነው። አሃሃሃ... ብቻዬን አይደለሁም ማለት ነው አልኩ።

እንደ ፔፐሮች ወግ ጸሃፊው ምስጋናውን ምኑን ካቀረበ በኋላ Abstract ብሎ የከተባት ነገር ቀልቤን ወሰደቺው። ''This study intends to find out the influences of exposure to pornography among young people in Addis Ababa.'' ብሎ ይጀምራል። እኔስ ይኸንኑ አይደል የፈለኩት ታድያ ብዬ ፔፐሯን መደዳ ወደታች አንዴ ሰለቀጥኳት…

90 ገጾቿን ካነበብኩ በኋላ እውነት ለመናገር ፔፐሯ አላረካቺኝም። አንደኛ የተጻፈችው በ2007ዓ.ም ነው። 2007 ማለት ደሞ ኢንተርኔት፣ በሰፈር አንድ ቦታ ተፈልጎ፣ በደቂቃ ብር ተከፍሎና ሰው ሁሉ የምንጠቀመውን እያየብን የምናገኘው ነገር ነበር። በዚያ ዘመን ወጣቱ ፖርን የሚያየው የሰፈር ፊልም ቤቶች ውስጥ በዛ ሰዓት እዛ ከተገኙ ሰዎች ጋር በመታደም ነበር። Privacy ወፍ። ፔፐሯ ላይ እንደውም የያኔ ወጣቶች ፖርን ሲያዩ erection እንደሚያጋጥማቸው ይገልጻሉ። HAHAA ወይ erection... ያሁን ዘመን ወጣት በአንድ እጁ ስልኩን ይዞ በአንድ እጁ በሶውን ካልጨበጠ መች ይሆንለታል። እና ፖርን ቁጭ ብሎ እንደ Avengers ሊያይ ነው? ለምን አትቀብረውም። ደግሞ ፔፐሩን የጻፈው የማስተርስ ተማሪ እየዞረ ጥያቄ ያቀረበላቸው የፖርን ተጠቃሚያን በአብዛኛው በአስራዎቹ መጨረሻ እና በሃያዎቹ መጀመሪያ ያሉ ናቸው። አብዛኞቹ ፖርን ብዙ ነገር አስተምሮናል፣ ይበል ይቀጥል የሚሉ ናቸው። ወይ ተማሪ ወይ ትምህርት ሳይሳካላቸው የቀሩ dropouts ስለሆኑ ፖርን ዝም ብሎ የጊዜ ማሳለፊያ መዝናኛ ነገር እንደሆነ እንጂ በህይወታቸው ላይ ያሳደረውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንዲህ ነው ብለው በጥልቀት መመርመር የሚችሉ ሰዎች አይደሉም። ፖርን የማይጠቀሙት ተጠያቂዎች ደግሞ እንደሁሌው የፖርንን አስጸያፊነት ከኃይማኖታቸው ከባህላቸው ከህይወታቸው አገናኝተው ይገልጻሉ ከዛ ጸሃፊው ፖርን ጥሩም ነው መጥፎም ነው በሚል ግራ መጋባት ሆኖ አንዳንድ የመፍትሄ ሃሳቦች አንስቶ ይጨርሳል።

አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት የፖርን ተጠቃሚዎች አሉ የሚለው ጥያቄዬ ስላልተመለሰልኝ ወደ ጋሽ GOOGLE ተመለስኩ። ከቅድሙ ፔፐር ዝቅ ብሎ ያለ አንድ መረጃ አይኔን ሳበው። '’Ethiopia ranked 4th in the world in searching "sex" in Google in 2013, Addis Ababa first followed by Amhara region and Dire Dawa.’’ ይላል። ሳስተውለው የFaceBook ፖስት ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት ከዓለም ዝቅተኛዎች ተርታ የምትመደብ ሆና ሳለ በዚህ እንዲህ ከታወቀች የሆነ ነገር አለ ማለት ነው ብዬ የመረጃውን እውነተኛነት ለማጣራት የራሴን ምርመራ ማካሄድ ጀመርኩ። ላለማንዛዛት GOOGLE ላይ በ2023 January ወር XNXX የሚባለው porn site ብቻ ወደ 10 ሚሊዮን ጊዜ በኢትዮጵያ search ተደርጓል። ይህ አስደንጋጭ ቁጥር ነው።

የድሮዉ የሚያስቀው ገና ከእንግሊዝኛም sex የምትለዋን ቃል ብቻ የሚያውቅ ሃበሻ GOOGLE ላይ ገብቶ እሷኑ search በማረግ ማጨናነቁ ነው። አሁን የት ቦታ ምን እንደሚገኝ እየገባው መጥቶ እነ XNXX የወጣቶቻችን የቀን ማሳረጊያ ሆነዋል። ወገኖቼ እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገው አንድ ሳይንስ ያረጋገጠው እውነታ ቢኖር ፖርን ከብዙዎቹ ገዳይ አደንዛዥ እጾች የማይተናነስ ሱስ የማስያዝ እና ሰውን ወደተበላሸ ባህሪ የሚዳርግ ክፉ ነገር መሆኑን ነው። ነገር ግን ይህን ባለማስተዋል ብዙ እየተጎዳንበት ነው። እኔ ከዚህ በተቃራኒ በመቆም መታገል እፈልጋለሁ። እኛ ሃገር እንግዲህ ብዙ ጊዜ ሰው ላይ የማንወደው ነገር ስናይ ስራችን ማጥላላትና ማንቋሸሽ እንዲሁም መፍረድ ብቻ ይሆንና ምንም መፍትሔ ሳናመጣ እንዲያውም ችግሩን አባብሰን እንሄዳለን። አሁን ግን በአእምሮ ሆነን እስኪ ይህን ነገር እንወያይበትና ወደ መፍትሔ እንምጣ ስል ይህችን ተከታታይ ጽሑፍ ጀመርኳት። እስከ ቀጣዩ፣ ቸር ቆዩ...

Comments (1)
No comments yet